ኢትዮጵያ የነዳጅ የተፈጥሮ ጋዝና ኃብቷን ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች ነው

101

መጋቢት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በፍለጋና በቁፋሮ የተገኙ የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ኃብቷን አካባቢያዊና ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት በማረጋገጥ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች መሆኗን የማዕድን ሚኒስቴር ገለጸ።

የማዕድን ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል የተፈጥሮ ጋዝ የኃብትና የኢኮኖሚ አዋጭነት ጥናት ለማካሄድ ከአሜሪካ ከዘርፉ ኩባንያ ጋር ዛሬ ሥምምነት ተፈሯርሟል።

ሥምምነቱን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ታከለ ኡማና የኔዘርላንድስ ስዌልና አሶሼትስ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ወልፍ ፈርመውታል።

የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በጥናትና በቁፋሮ የተገኙ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ኃብት ውጤቶችን ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ ነው።

የነዳጅና የተፈጥሮ ኃብቱን ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ የተጠናና ዘላቂ ጥቅምን ያመዛዘነ እንዲሆን ዓለም አቀፍ ማረጋገጫ ለማግኘትም መታቀዱ ጠቁመዋል።

ይህንንም ተከትሎ ሚኒስቴሩ ኔዘርላንድስ ስዌልና አሶሼትስ ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ዛሬ ሥምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

ኩባንያው በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ተፋሰስ 3 ሺህ 500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ የተሰሩ የፍለጋና የጥናት ውጤቶችን መነሻ በማድረግ በተፋሰሱ ያለውን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ኃብት መጠን የሚያሳውቅና ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱን የሚያሳይ ጥናት እንደሚያካሂድ ተናግረዋል።

ጥናቱ  ለአራት ወራት የሚካሄድ ሲሆን የተፈጥሮ ጋዙን ከፊሉን ለማዳበሪያና የተቀረውን ደግሞ ለኃይል በማዋል የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንደሚጠቀም ገልጸዋል።

የኔዘርላንድስ ስዌልና አሶሼትስ ኩባንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ወልፍ በበኩላቸው ኩባንያው የሚያካሂደው ጥናት ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።

የማዕድን ኃብትን በመጠቀም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት በሚደረገው ጥረት የአዋጭነት ጥናቱን በአግባቡ ለመወጣት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈፃሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን፣ የኩባንያው አመራሮችና የማዕድን ሚኒስቴር አመራሮች ተገኝተዋል።

ኩባንያው በዘርፉ ታዋቂ ባለሙያዎችን የያዘና ለበርካታ አገራት በመሥራት ልምድ ማካበቱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ  የነዳጅ ፍለጋ  ታሪክ ከ1970 የሚጀምር ሲሆን የተለያዩ አገራት ኩባንያዎች በሶማሌ ክልል በኦጋዴን አካባቢ የነዳጅ ፍለጋና ልማት ሥምምነቶችን አድርገው የጥናትና የቁፋሮ ሥራዎች ሲያካሂዱ  መቆየታቸውን ከማዕድን ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም