በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው

77

አዲስ አበባ መጋቢት 13/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የዓለም የውሃ ቀንን ''ትኩረት ለከርሰ ምድር ውሃ ሀብታችን '' በሚል መሪ ሃሳብ ለ30ኛ ጊዜ አክብሯል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ ከ12 ተፋሰሶች የውሃ ሃብቷን የምታገኝ ሲሆን ያለውን የውሃ ሃብት በተገቢው ሁኔታ ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

በሚኒስቴሩ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዴንጋሞ፤ በተለይ የከርሰ ምድር ውሃን በአግባቡ በመጠቀም ድርቅና የውሃ እጥረት ችግርን ለማቃለል በጥናት ታግዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከ122 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዮብ በላይ የገጸ-ምድር ውሃ ያላት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳታውል ቆይታለች።

በከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ዙሪያ እየተደረገ ያለው ጥናት ግን ገና አልተጠናቀቀም ብለዋል።

በቀጣይ ዓመታት በአጠቃላይ ያለውን የከርሰ-ምድር ውሃ ለመጠቀም ጥናቶቹ የሚቀጥሉ መሆኑን በማንሳት ለዚህም ከፍተኛ ቴክኖሎጂና ሃብት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የከርሰ ምድር ውሃ ጥናትና ዲዛይን ቡድን መሪ  መኳንንት ኃይሌ፤ በከርሰ ምድር ውሃ ሀብትና አጠቃቀም ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ አንስተዋል።  

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ ፍለጋ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን ጠቅሰው፤ ሃብቱን በማቀናጀት ጥቅም ላይ ለማዋል በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።

በከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ተጠቃሚ ለመሆን በሚኒስቴሩ በኩል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆኑም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም