የጋምቤላ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር ኡኬሎ ኝጌሎ ስረአተ ቀብር ተፈጸመ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር ኡኬሎ ኝጌሎ ስረአተ ቀብር ተፈጸመ

ጋምቤላ፣ መጋቢት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር ኡኬሎ ኝጌሎ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ።
አቶ ኡኬሎ ኝጌሎ ባደረባቸው ድንገተኛ ህመም በ58 ዓመታቸው መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አቶ ኦኬሎ የቀብር ስነ ስርአት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ዛሬ ተፈጽሟል።
የክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት በቀድሞው ርዕሰ መተዳድር አቶ ኡኬሎ ኝጌሎ ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጾ፤ ለቤተሰቦቻቸውና ወደጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።
አቶ ኡኬሎ ኝጌሎ ከአባታቸው ከአቶ ኝጌሎ ኡላምና ከእናተቻው ከወይዘሮ ኝዊሪ ታታ ህዳር 18 ቀን 1958 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በኢሊያ ቀበሌ መወለዳቸው በህይወት ታሪካቸው ተመላክቷል።
አቶ ኡኬሎ በ1978 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ በ1979 ዓ.ም በጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም በመምህርነት የሰለጠኑ ሲሆን በጋምቤላ መምህራን፣ ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ደግሞ በዲፕሎማ ተመርቀዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአልፋ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በፌዴራሊዝምና መልካም አስተዳደር ዘርፍ ተከታትለው አጠናቀዋል።
አቶ ኡኬሎ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ዓመት ያህል በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን በሽግግር መንግስት ወቅት የኢታንግ ልዩ ወረዳ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል።
እንዲሁም ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ዓመት ያህል የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ሹም ሆነው አገልግለዋል።
አቶ ኡኬሎ ከነሐሴ 1989 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ዓመት ያህል የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር፣ የጋህነን ስራ አስፈፃሚና ሊቀመንበር በመሆን ህዝባቸውን ያገለገሉ አመራር እንደነበሩ የህይወት ታሪካቸው ያሳያል።
አቶ ኡኬሎ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የህግ አማካሪ፣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ የክልሉ ህብረት ስራ ማደራጃና ማስፋፊያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።
አቶ ኦኬሎ ባለትዳርና የሶስት ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበሩ።