የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

257

አዳማ ፤ መጋቢት 13/2014(ኢዜአ) የጨፌ ኦሮሚያ ስድስተኛ የስራ ዘመን አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ ።

ጨፌው በሁለት ቀናት ቆይታው ካፀደቃቸው መካከል የክልሉን የልማት ድርጅቶች በአዲስ መልክ ለማደረጀት የተዘጋጀውን ፣ የአካባቢን ሰላም ተደራጅቶ ለመጠበቅ የሚያስችለውን "ጋቸነ ሲርና" እንዲሁም "ቡሳ ጎኖፋ" የኦሮሞ ህዝብ የመተጋገዝና መረዳዳት ባህል አዋጆች ይገኙበታል።

የጨፌ አባላት ስነ ምግባርና አሰራር ለመወሰን የተዘጋጀን ደንብንም ተወያይቶ ያጽደቀው ሌላው የመረሐግብሩ አካል ነው።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ  ለጨፌው በሰጡት ማብራሪያ፤   የክልሉ መንግስት የልማት ድርጅቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ውስጥ የላቀ ሚና መጫወት እንዲችሉ በአዲስ መልኩ ማደራጀት አስፈልጓል።

በተለይም በመንግሥት ባለቤትነት ብቻ የተወሰኑ የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል በማዛወር ውጤታማነታቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደሆነም ተናግረዋል ።

የ"ጋቸነ ሲርና " አዋጅ ያስፈለገው የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥና የህዝቡ ደህንነት አስተማማኝ ዋስትና እንዲኖረው ከማስቻል ባለፈ የፀጥታ መዋቅሩን በሰው ሃይል ይበልጥ ለማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል።

"ቡሳ ጎኖፋ ` አዋጅም የኦሮሞ ህዝብ ወደ ነበረበት ቱባ ባህልና እሴቱን ጠብቆ ተቋማዊ በሆነ መንገድ እንዲረዳዳና እንዲደጋገፉ ነው ብለዋል።

አዲሱ የክልሉ መንግስት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቀድሞ የነበረውን አዋጅ ቁጥር 181/2005 የሚተካ መሆኑ ተገልጿል።

ይህን አስመልክተው የጨፌ ኦሮሚያ የአስተዳደርና ህግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ናስር ሁሴን፤ የቀድሞ አዋጅ ሀብቱን የሚያስተዳድረው መንግስት ብቻ መሆኑን የሚደነግግ በመሆኑ ክፍተትና ውስንነት ነበረበት ብለዋል።

አዲሱ አዋጅ ሀብቱን በከፊል ለግል ለማዛወር የሚፈቅድ ከመሆኑም ባለፈ የክልሉ መንግስት የልማት ድርጅቶች የነፃ ገበያ መርህን ተከትለው እንዲሰሩና ገበያውን በማረጋጋት ሚናቸውን እንዲጫወቱ ያለመ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወይዘሮ አዱኜ አህመድ ናቸው።

የቡሳ ጎኖፋ አዋጅ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ወደ ነበረበት ማንነት እንዲመለስ፣ የነበረው የመረዳዳትና መተጋገዝ ባህል ተቋማዊ እንዲሆን ለማስቻል ዓላማ ያደረገ  መሆኑን ጠቅሰው፤ በድርቅ የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማገዝ ራሱን የቻለ አሰራርና የህግ ማዕቀፎች ለማበጀት እንደሆነም አስረድተዋል።

ጨፌው የክልሉን የስራ አስፈፃሚ ያለፉት ሰባት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት በማዳመጥና በጥልቀት ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ ማፅደቁም ተመልክቷል።

ጨፌው  የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን ሹመት በማፅደቅ መረሐግብሩን አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም