ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ወስደዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ

104

መጋቢት 13/2ዐ14 (ኢዜአ) በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ይዞታ በሌላቸው ግለሰቦች ስም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ወስደዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ ሶስት ተከሳሾች ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ታዘዘ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው ዛሬ ትእዛዙን የሰጠው።

ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ቦሌ አራብሳ በሚባለው አካባቢ  ባለይዞታ ባልሆኑ ግለሰቦች ስም ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ተገቢ ያልሆነ የካሳ ክፍያ ወስደዋል ተብለው በመጠርጠራቸው ነው።

የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ የቦሌ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽህፈት ቤት የካሳ ይዞታ ማረጋገጥና ማጽደቅ ዘርፍ ሰራተኞች የነበሩ 21 ተከሳሾች ናቸው።

በ1ኛ ተከሳሽ አማካኝነት በቦሌ አራብሳ አካባቢ በውሃና ፍሳሽ ተቋም ለሚሰራ ውሃ ማጣሪያ ፕሮጀክት ስራ ይዞታ ከሌላቸው ግለሰቦች ጋር በዘመድና በጥቅም በመተሳሰር የመሬት ይዞታ እንዳላቸው ተደርጎ ስም ዝርዝር መግባቱ ተጠቅሷል፡፡

በዚህም ግለሰቦቹ በይዞታ ባለቤትነት በሀሰት የተመዘገቡ ቤተሰብና የተለያዩ ግለሰቦችን ውክልና በመውሰድ ይዞታ በማረጋገጥ፣ የይዞታ ካሳ በማጽደቅና፣ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተገባ ካሳ ገንዘብ በመውሰድ ተከሰዋል፡፡

ዓቃቤ ህግም እንደተሳትፎ ደረጃቸው የካቲት 30 ቀን 2014  ዓ.ም የከባድ ሙስና ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የቀረበባቸውን ክስ ለማንበብና ያልቀረቡ ቀሪ 18 ተከሳሾች እንዲቀርቡ የሰጠውን ትዕዛዝ ውጤት ለመጠባበቅ ዛሬ ተሰይሞ ነበር።

ሆኖም የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ  ወረዳ 06 ስራ አስፈጻሚ አቶ ገረመው ግዛቸውን ጨምሮ 18ቱ ተከሳሾች ችሎት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ለዛሬ እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ የተሰጠው ፖሊስ መጥሪያው መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም የደረሰው መሆኑን ጠቅሶ የጊዜ እጥረት ስላጋጠመው ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን በችሎቱ ተገልጿል ።

ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ ያልቀረቡ 18 ተከሳሾችን ፖሊስ ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

አቃቢ ሕግ በበኩሉ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት 14ኛ ተከሳሽ በቀለ ገረሱ፣15ኛ ተከሳሽ  ጫላ አለሙና 19ኛ ተከሳሽ ተስፋዬ አለሙ ዋስትና በሚያስከለክል አንቀጽ መከሰሳቸውን በመጠቆም ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ጠይቋል።

በመሆኑም ሶስቱም ተከሳሾችን ከዛሬ ጀምሮ  ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩና በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያቸውን በጽሑፍ እንዲያስገቡ ነው ፍርድ ቤቱ ትአዛዝ የሰጠው።

በቀጣይም ፖሊስ ቀሪ ተጠርጣሪዎችን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ለመጋቢት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም