አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን

73

መጋቢት 13/2014/ኢዜአ/ አገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ሐሳቦች የሚንጸባረቁበትና ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ የእናት ፓርቲ እንዲሁም የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ገለጹ።

የእናት፣ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ኃላፊዎች አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጌትነት ወርቁ እንደገለጹት፤ ፓርቲያቸው አገራዊ ምክክሩን በምዕተ-ዓመት አንድ ጊዜ የሚገኝ እድል አድርጎ ወስዶታል።

ምክክሩ የፓርቲ፣ የግለሰብና የገዥው ፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የአገርና የትውልድ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ፓርቲያቸው ለውጤታማነቱ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ አንድነት፣ ልማትና ብልጽግና የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ በሚያደርጉን ላይ መነጋገር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

አገራዊ ምክክሩ የቀጣይቷን ኢትዮጵያ  የሚወስንና መልካም ነገር ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም የተሻለ ሐሳብ ጎልቶ እንዲወጣ ፓርቲው ይሰራል ብለዋል።

እናት ፓርቲ በአገራዊ ጉዳይ ላይ በሰላማዊና አዎንታዊ መንገድ በመሳተፍ የአገራዊ ምክክሩ ሂደት እስከ መጨረሻው ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን እንደሚያደርግ ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል።

የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር ሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ዘኑር አብዱልውሃብ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን ፓርቲው እንደሚያምን ገልጸዋል።

ለረዥም ዓመታት በማኅበራዊ፣ በምጣኔ ኃብትና በፖለቲካ ጉዳዮች ሥር የሰደዱ ችግሮችን እንደሚፈታ በማመን በውይይቱ ከመሳተፍ በተጨማሪ ለውጤታማነቱ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ለሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ጦርነት፣ ሞት እና መፈናቀል ምክንያቶችን ከምንጩ ለማድረቅ ውጤታማ ምክክር ማድረግ የህልውና ጉዳይ መሆኑን አማካሪው አስገንዝበዋል።

አገር በመካረርና በመሳሳብ የሚገነባ ባለመሆኑ በተዋረድ የሚደረጉ ምክክሮች በሐሳብ ፍጭት እንዲካሄዱ አባላቶቻቸውን እያስገነዘቡ መሆኑን የፓርቲው ኃላፊዎች ጠቁመዋል።

ብሔራዊ መግባባት አገርን የማጽናት ጉዳይ በመሆኑ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ በማስቀመጥ ሁሉም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ምክክሩን የሚያስተባብሩ 11 ኮሚሽነሮች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. መሾማቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም