የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

97

አዳማ፤ መጋቢት 12/2014(ኢዜአ) የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 1ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዳማ ከተማ መካሄድ ጀመረ።

በአዳማ ጨፌ አዳራሽ በተጀመረው ጉባኤ ላይ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱረህማን እንደተናገሩት፤ የጨፌ አባላት ድርቅና የኑሮ ወድነት፣ ፀጥታና ልማት ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የክትትልና ቁጥጥር ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።

የክልሉ የፀጥታ ችግር አሁንም የክልሉን መንግስትና የጨፌውን ልዩ ትኩረት የሚፈልግ ነው ያሉት አፈጉባኤዋ፤ ህዝቡ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሰላሙን ማስጠበቅ እንዳለበት አመልክተዋል።

የንግድ ስርዓቱን በማዛባት ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተቸገረ በመሆኑ ጉባኤው ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት ።

የመሬት ወረራ፣ የስራ አጥነትና ሌሎችንም ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለዋል።

ጨፌ ኦሮሚያ የወከለውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከምን ጊዜውም በላይ እየሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉን የስራ አስፈፃሚ የመከታተልና የመቆጣጠር እንዲሁም የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ ጉዳዮች በጉባኤው ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆናቸንም አመላክተዋል።

እንደ አፈ ጉባኤዋ ገለጻ፤ በግብርና፣ በበጋ መስኖ ልማት፣ ድርቅን ለመቋቋምና በመልካም አስተዳደር ዙሪያዎች በቀጣይ የሚሰሩ ተግባራት እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ተጓተው የህዝብ ቅሬታ የሚቀርብባቸው ጉዳዮች የሚፈቱበት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

ጨፌው የክልሉን የስራ አስፈፃሚ አካል የስድስት ወራት ክንውን በመገምገም፣ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አዋጆችና ደንቦችን እንደሚጻደቅም እንዲሁ።

እንዲሁም የክልሉ መንግሥት የልማት ድርጅቶችን በአዲስ መልክ ለማቋቋም፣ "የቡሳ ጎኖፋ" የኦሮሞ ህዝብ የመረዳዳትና መደጋገፍ፣ ለሰላምና ፀጥታው "የጋቸነ ሲርናን" ለማደራጀት የተዘጋጁ ረቅቅ አዋጆችን መርምሮ እንደሚያጸድቅም አፈ ጉባኤ ሰዓዳ ጠቁመዋል ከዚህም ባሻገር የጨፌ አባላት ስነ ምግባር፣ አሰራርና ኃላፊነትን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ በጉባኤው እንደሚጸድቅ ተመልክቷል።

ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው የክልሉን መንግስት ያለፉት 7 ወራት የስራ አፈፃፀምን ጨምሮ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም