የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ረቂቅ አዋጆችና ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

61

ጋምቤላ፤ መጋቢት 11/2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት አንደኛ የስራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ጉባኤ አምስት ረቂቅ አዋጆችና የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን ውጤታማ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አሳስበዋል።

ጉባኤው የተጠናቀቀው የክልሉን የ2014 በጀት የግማሽ ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የኦዲት ቢሮ እቅድ አፈፃፀምና በቀጣይ ግማሽ ዓመት የተከለሰ እቅድ ላይ ተወያየቶ በማጽደቅ ነው።

እንዲሁም የክልሉን የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ጨምሮ አምስት ረቂቅ አዋጆችና የተለያዩ ሹመቶችን መርምሮ አጽድቋል።

የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የጸደቀውን አዋጅ ተከትሎም የአስፈፃሚ አካላት ሽግሽግ ተደርጎል።

በሽግሽጉ መሰረት ጉባኤው የሶስት ካቢኔ አባላት ሹመት ያጸደቀ ሲሆን የ18 የወረዳና የከፈተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ሹመትን መርምሮ አጽድቋል።

ጉባኤው የስነ- ምግባር ችግር ያለባቸውን ስድስት የወረዳና የከፈተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ከኃላፈነታቸው ያነሳ ሲሆን ሶስቱን ደግሞ ከደረጃ ዝቅ እንዲሉ ውሳኔ አሳልፏል።

የምክር ቤቱ አፈ- ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ "አመራሩ ባለፈው ግማሽ ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስፋትና ጉድለቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዘገብ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

"በተለይም አመራሩ የኑሮ ውድነት፣ የብልሹ አሰራር፣ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ የመጠጥ ውሃ ችግሮችን ለማቃለል በቁርጠኝነት ሊሰራ የገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።አመራሩ የወጣቶችና የሴቶችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ አፈ -ጉባኤዋ አሳስበዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በቀጣይ ግማሽ ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ውጤታማ እንዲሆኑ የክትትልና ቁጥጥር ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አፈ -ጉባኤዋ አስገንዝበዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም