በድሬዳዋ 710 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ ተወገደ -ፖሊስ

63

ድሬዳዋ መጋቢት 11/2014 /ኢዜአ/ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ  በቁጥጥር ሥራ የያዘውን 710 ኪሎ ግራም አደንዛዥ ዕፅ ማስወገዱን አስታወቀ።

እጹ  የነዋሪዎችን ጤንነት በማይጎዳ መልኩ  ከከተማው ወጣ ባለ ስፍራ በዛሬው እለት እንዲቃጠል መደረጉ ታውቋል።

የድሬዳዋ  ፖሊስ  የታክቲክ ምርመራ ዘርፍ ዳይሬክተር ምክትል ኮማንደር መሀመድ ኢብራሂም ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር በተለያዩ ጊዜያት ባካሄደው የቁጥጥር ሥራ የያዘው 710 ኪሎ ግራም አደንዛዥ እጽ እንዲወገድ ተደርጓል።

"በግምጃ ቤት ተከማችቶ የነበረ ካናቢስ የተሰኘ አደንዛዥ ዕጽ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ እንዲቃጠል ተደርጓል" ብለዋል   ገልጸዋል፡፡

"ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ድሬዳዋ ሲገባና ወደ ጅቡቲ ጭምር ዕፁን ለማጓጓዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በህግ ተገቢው ቅጣት ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤት ይገኛሉ" ሲሉም አክለዋል ፡፡

 የድሬደዋ ፖሊስ የሰው መግደል ልዩ ልዩ ወንጀሎች ዲቪዢን ሀላፊ ኢንስፔክተር ተመስገን ተስማ በበኩላቸው በከተማው የአደንዛዠ እፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዩኒቨርሲቲ፣ በኮሌጆችና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚደረገውን ቁጥጥር በማጠናከር ከሱስ ነጻ የሆነ አገር ገንቢና ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ግንዛቤን በማሳደግ እና አጥፊዎችን ለህግ በማቅረብ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

 "አደገኛ ዕፅ ዝውውር ከምንጩ ለማድረቅ ድንበር ዘለል ቅንጅት ጭምር በመፍጠር እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ  የድሬዳዋ  ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምክትል ማኦ ተሾመ ናቸው።

በፍትህ ሚኒስቴር የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሉቀን ካሳሁን በበኩላቸው "ለተለያዩ  ወንጀሎች መንስኤ እየሆነ የሚገኘውን የእጽ ዝውውርና ተጠቃሚነት  ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ካሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በተጓዷኝ በወንጀሉ ተሳታፊ የሆኑ የአደንዛዥ ዕፅ አብቃዮች፣ አዘዋዋሪዎችና ተጠቃሚዎች በህግ ተጠያቂ እየተደረጉ ናቸው" ብለዋል፡፡

ባለፉት 10 ዓመታት በወንጀሉ  ተሰማርተው በ145 መዝገቦች በተከሰሱ ላይ ከሶስት ወር እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን ጠቅሰዋል ።

ዘንድሮ በተመሣሣይ ወንጀል ተሰማርተው በቁጥጥር ሥር  በዋሉ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ ለማስወሰድ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም