ዳሽን ቢራ ፋብሪካ በገንዳ ውሃ ከተማ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የ100 ኩንታል ዱቄት ድጋፍ አደረገ

67

መተማ፣ መጋቢት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳሽን ቢራ ፋብሪካ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚከፋፈል 100 ኩንታል የምግብ እህል ዱቄት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በከተማዋ የዳሽን ቢራ ወኪል አከፋፋይ አቶ ሲሳይ መከተ አስረክበዋል።

በወቅቱም እንደገለጹት፤ ድጋፉ 400 ሺህ ብር ወጪ የተደረገበት ነው።

ፋብሪካው በህልውና ዘመቻ ጀምሮ የተለያየ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በገንዳ ውሃ ከተማ ያደረገውን አይነት ድጋፍ በሁመራ፣ ደባርቅ፣ እብናትና ደሴ ከተሞች በቅርቡ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ፋብሪካው ከድጋፍ በተጨማሪ  በከተማው ለትምህርት ቤት ግንባታ አንድ ሚሊዮን ብር ለመለገስ  ቃል መግባቱንም ተናግረዋል።

የገንዳ ውሃ ከተማ ተወካይ ከንቲባ አቶ ጥላሁን ተፈሪ በበኩላቸው ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ከ800 በላይ ለሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል።

ገበያውን ለማረጋጋት መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ባለሀብቶችም የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም