የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ሕጻናት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ሕጻናት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል
መጋቢት 11/2014 /ኢዜአ/ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት ትምህርትን ጨምሮ በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የሕጻናቱ ወላጆች ጠየቁ።
በዲቦራ ፋውንዴሽን "ዓለም አቀፍ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት ቀንን" በማስመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ የእግር ጉዞ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በእግር ጉዞ ላይ የተሳተፉ የአእምሮ አድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት ቤተሰቦች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት ተገቢውን ትኩረት አላገኙም።
በአገሪቱ አስፈላጊውን ያክል የአካቶ ትምህርት አለመኖሩን ጠቁመው የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም መንግሥትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለእነዚህ ሕጻናት ትምህርት ቤት በመክፈት ማኅበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ኅብረተሰቡም የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት ያለመድሎና መገለል በተለያዩ ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆን የበኩሉን ደርሻ መወጣት እንዳለበት ጠይቀዋል።
የዲቦራ የፋውንዴሽን መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው፤ የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት እራሳቸውን እንዲችሉ እየሰራን ነው ብለዋል።
የአእምሮ እድገት እክል ያለባቸው ሕጻናት በማኅበራዊ ዘርፎች ላይ ያለምንም ገደብ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አካታችነትን በአግባቡ ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰራ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
ፋውንዴሽኑም በሚቀጥለው ዓመት የአእምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሕጻናት የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ለመስጠት እቅድ መያዙንም አቶ አባዱላ ተናግረዋል።
የተለያዩ ጤና ተቋማት ችግሩ ላለባቸው ሕጻናት ሕክምና በነጻ እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመው ሌሎችም የጤና ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍልና የሚመለከታቸው አካላት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ፋውንዴሽኑን በመደገፍ ሕጻናትን ማገዝ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ ከእዕምሮ ውስንነት ጋር የተወለዱ ሕጻናትን ምርታማ በሚሆኑበት ምቹ አውድ ለመፍጠር በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በአገሪቱ በአዕምሮ እድገት ውስንነት ጋር ለተወለዱት ህፃናት ላይ የተሰራ ሥራ እምብዛም እንደሆነ ጠቁመው በቀጣይ በአገር አቀፍ ደረጃ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ በአዕምሮ እድገት ውስንነትም ሆነ በሌሎች ከአዕምሮ ጋር በተያያዘ ለሚሰሩ ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ዶክተር ሊያ አረጋግጠዋል።
በ2011 ዓ.ም የተመሰረተው ዲቦራ ፋውንዴሽን የአእምዕሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናት ትኩረት እንዲያገኙና በአካታችነት ዙሪያ ግንዛቤ እየፈጠረ ነው።
ፋውንዴሽኑ አሁን ላይ ሕጻናቱን ታሳቢ ያደረገ በአይነቱ የመጀመሪያ የትምህርትና የሥነ-ጥበብ ማዕከል በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ እያስገነባ መሆኑም ተገልጿል።
በቀጣይም ወርሃዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ለማካሄድ ማቀዱም ተገልጿል፤ ፋውንዴሽኑ ከአንድ ሺህ በላይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናትን በስሩ አቅፏል።
ዓለም አቀፍ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት ቀን "አካታችነት መብት እንጂ ችሮታ አይደለም" በሚል መሪ ኃሳብ ተከብሯል።