ለ6ኛው ዕዝ የሠራዊት አባላት የሜዳይ ሽልማትና የማዕረግ ዕድገት የመስጠት ሥነሥርዓት እየተካሄደ ነው

86

መጋቢት 11 ቀን 2014(ኢዜአ) በህልውና ዘመቻው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ለ6ኛ ዕዝ አባላት የሜዳይ ሽልማትና የማዕረግ ዕድገት የመስጠት ሥነሥርዓት በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በሥነሥርዓቱ ላይ የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሰለሞን ኢተፋንና የዕዙ ዋና አዛዥ ሜጄር ጀነራል ተስፋዬ ወልደማሪያምን ጨምሮ የሠራዊቱ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።

በህልውና ዘመቻው የተሻለ አስተዋጽኦ ላበረከቱና ላቅ ያለ ሚና ለተጫወቱ የዕዡ አመራሮችና አባላት የሜዳይ ሽልማትና የማዕረግ ዕድገት ይሰጣል።

የ6ኛ ዕዝ የኢንዶክትሬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሻለቃ ዮሴፍ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት በአሸባሪው ህወሓት ሀገር እንዳይፈርስ በተካሄደው የህልውና ዘመቻ ዕዡ አንጸባራቂ ድል አስመዝግቧል።

ሠራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ባካሄደው ዘመቻ በሽብር ቡድኑ ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ አድርሶ መውጫ ቀዳዳ እንዳሳጠውም ገልጸዋል።

ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው ኢትዮጵያን ከመፍረስ የታደጉ ጀግኖች ምን ጊዜም ሲወሱና ሲወደሱ እንደሚኖሩ አመልክተዋል።

ሻለቃ ዮሴፍ የህልውና ዘመቻው በአጭር ጊዜ በድል እንዲጠናቀቅ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

በሜዳይ ሽልማትና በማዕረግ ዕድገት የመስጠት ሥነሥርዓቱ ላይ ለሠራዊቱ ድጋፍ ያደረጉ ባለሃብቶች፣ባለድርሻ አካላትና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ አመራሮችና ተወካዮችም ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም