ኢትዮጵያ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳሊያ ሰንጠረዥ እየመራች ነው

513

መጋቢት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ)ኢትዮጵያ በሰርቢያ ቤልግሬድ እየተካሄደ ባለው 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳሊያ ሰንጠረዥ እየመራች ነው።በሻምፒዮናው ዛሬ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።

ትናንት ማምሻውን በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት በበላይነት አጠናቀዋል።

አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ 3 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ ከ19 ማይክሮ ሰከንድ በርቀቱ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን በመስበር አሸንፋለች።

አትሌት አክሱማዊት አምባዬ 4 ደቂቃ ከ2 ሰከንድ ከ29 ማይክሮ ሰከንድ ሁለተኛ ስትወጣ ፤አትሌት ሂሩት መሸሻ 4 ደቂቃ ከ3 ሰከንድ ከ39 ሰከንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።

ኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ በ3000 ሜትር ሴቶች በአትሌት ለምለም ኃይሉ አማካኝነት የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን፤አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

ውጤቱን ተከትሎ የሻምፒዮናውን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅ አንድ ብር፤ ሁለት ነሐስ በድምሩ አምስት ሜዳሊያዎች በማግኘት በአንደኝነት እየመራች ነው።

በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጨረሻ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።ከቀኑ 8 ሰአት ከ5 ደቂቃ በ3000 ሜትር ወንዶች አትሌት ሰለሞን ባረጋና አትሌት ለሜቻ ግርማ ይሳተፋሉ።

አትሌት ሰለሞን እ.አ.አ በ2018 በዩናይትድ ኪንግደም በርሚንግሐም በተካሄደው 17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3000 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን፤አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ የውድድሩ አሸናፊ እንደነበር አይዘነጋም።

ከምሽቱ 2 ሰአት ከ5 ደቂቃ ላይ በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት ሃብታም አለሙና አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

ከምሽቱ 2 ሰአት ከ30 ደቂቃ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች አትሌት ሳሙኤል ተፈራና አትሌት ታደሰ ለሚ ይሳተፋሉ።

አትሌት ሳሙኤል እ.አ.አ በ2018 በዩናይትድ ኪንግደም በርሚንግሐም በተካሄደው 17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1 ሺህ 500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረ ሲሆን፤ዛሬም በሻምፒዮናው በርቀቱ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይሮጣል።

18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል።በቤልግሬድ እየተካሄደ ያለው ሻምፒዮና እ.አ.አ በ2020 መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሁለት ዓመት መራዘሙ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም