የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመግቢያ ነጥብ የተወሰነው የተቋማቱን የመቀበል አቅም ታሳቢ በማድረግ ነው

274

አዲስ አበባ መጋቢት 09/2014(ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የመግቢያ ነጥብ የተወሰነው የተቋማቱን የመቀበል አቅም ታሳቢ በማድረግ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በጸጥታ ችግር ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ሁለት ጊዜ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች በመኖራቸው ምክንያት የተወሰነ የእርማት ስህተት መፈጠሩም ነው የተገለጸው ፡፡

በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ሀገራዊ የሰላም እጦት በስርዓተ ትምህርቱ ላይ በፈጠረው ችግር የፈተና መስጫ መርሃ ግብር ላይ መዛባት መፍጠሩ ይታወቃል፡፡

በዚህም በ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች የፈተና መርሃ ግብር ወደ 2014 ዓ.ም ተዛውሮ የመጀመሪያው ዙር ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ቀን እንዲሁም ሁለተኛው ዙር ከጥር 27 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የ10ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና በመቅረቱ ምክንያት በዘንድሮው ዓመት በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ፈተና ወስደዋል፡፡  

በዘንድሮው ዓመት ለፈተና የቀረቡት ተማሪዎች ቁጥር 598 ሺህ 679 መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ አሃዝ በ2012 ዓ.ም ከተፈተኑ 321 ሺህ ተማሪዎች ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ጨምሯል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ምክንያት ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 50 በመቶ ውጤት አስመዝግበው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት የሚችሉት 45 በመቶ ሲሆኑ፤ ወደ መንግስት ተቋማት የሚገቡት ደግሞ 25 በመቶ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ካሉት 47 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በትግራይ ክልል የሚገኙት አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን እንደማይቀበሉና ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩትም ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ይህም የቅበላ አቅማችንን ወደ 43 ዩኒቨርሲቲዎች ዝቅ አድርጎብናል ብለዋል፡፡

አራቱ ዪኒቨርሲቲዎች እስከ ተመራቂ ድረስ ያሉ ጨምሮ በዓመት እስከ 48 ሺህ ተማሪዎችን ያስተናግዱ ስለነበር፤ ይህ በመቅረቱ በቀሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

"የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲያችን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች 50 በመቶ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸው ያስቀምጣል" የሚሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152/2011 መሰረትም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት መቁረጫ እንዴት እንደሚወሰን በግልጽ ተቀምጧል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት 147 ሺህ ተማሪዎች ወደ መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባታቸውን አስታውሰው፤ በዘንድሮው ዓመት ደግሞ 152 ሺህ ተማሪዎች የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን ይቀላቀላሉ ብለዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት ተማሪዎችን የሚቀበሉ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ቋማት ቁጥር ወደ 43 ዝቅ ቢልም ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር በአምስት ሺህ መጨመሩን አብራርተዋል፡፡

"በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በመፈተናቸው እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቅበላ አቅም በመቀነሱ ችግሩን የሰፋ አስመስሎታል፤ ነገር ግን የመጨረሻ አቅማችንን አሟጠን ተጠቅመን የተማሪዎችን ቁጥር አሳድገናል" ብለዋል፡፡    

ኢትዮጵያ በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች እየተፈተነች ተማሪዎች በሁለት ዙር ቢፈተኑም ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በጥቂቱም ቢሆን የውጤት መሻሻል እንዳለ ተገንዝበናል ብለዋል ሚኒስትር ድኤታው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአንድ ትምህርት ቤት ብዙ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ አምጥተው በሌላ ትምህርት ቤት ጥቂት መሆናቸው የተለመደና የትምህርት ቤቶችን አቅም የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

በጸጥታ ችግር ምክንያት በሁለተኛው ዙር ከተፈተኑ 53 ሺህ 997 ተማሪዎች መካከል በ80 በመቶ የሚሆኑን ከአማራ ክልል ሲሆን ቀሪዎቹ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋርና ኦሮሚያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የእነዚህ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማለፍ ምጣኔ 50 በመቶ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር የነበሩት ምጣኔ ደግሞ 44 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህ ደግሞ በጸጥታና ተያያዥ ጉዳዮች በተማሪዎች ላይ የደረሰ የከፋ ተጽዕኖ እንደሌለ ያሳያል ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ የማለፍያ ነጥቡም ይሄንን ታሳቢ አድረጎ የተወሰነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ በበኩላቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና ከሰው ንክኪ ነፃ ሆኖ በጸጥታ ሀይሎችና በደህንነት ካሜራ እየተጠበቀ መታረሙን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ፈተናውን በሁለት ዙር መስጠት አስገዳጅ በመሆኑ በፈተና እርማቱ ላይ አጠራጣሪ ጉዳዮች ተከስተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በሁለት ዙር ፈተና ከወሰዱ 598 ሺህ 679 ተማሪዎች መካከል 91 በመቶ የሚሆኑት በመጀመሪያው ዙር የተፈተኑ ቢሆንም በጸጥታ ምክንያት ከሁለት ቦታ የተፈተኑ መኖራቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

ይህም ከአንድ ትምህርት ቤት በሁለቱም ዙር የተፈተኑ ተማሪዎችን ውጤት አንደኛውን በትክክለኛው ኮድ ሌላውን ደግሞ በተሳሳተ ኮድ እንዲታረም አድርጎታል ብለዋል፡፡

በዚህም ከ500 የማይበልጡ ተማሪዎች ሁለት ጊዜ በመፈተናቸው የተፈጠረ የማሽን ስህተት መሆኑ ታይቶ እንዲስተካከል ተደርጓል ብለዋል፡፡

የፈተና እርማቱን ቅሬታ በተመለከተ "በወቅቱ መላሽ አልተሰጠም፤ የተሰጠው ምላሽም አጥቃቢ አይደለም" የሚል ቅሬታ እንደሚቀርብም ተናግረዋል፡፡

የተፈጠረው ችግር ፈተናው በሁለት ዙር በመሰጠቱ እንጂ በሌላ ምክንያት አይደለም፤ ለተፈጠረው ስህተት ግን ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም