ኮርፖሬሽኑ በግማሽ ዓመት ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ አገኘ

77

አዲስ አበባ መጋቢት 09/2014(ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በግማሽ ዓመት ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የስድስት ወር እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻው ደምሴ፤ ኮርፖሬሽኑ ከገበያ ማረጋጋት ሥራ ጎን ለጎን ትርፋማ ለመሆን እየሰራ ነው ይላሉ።

በዚህም በግማሽ ዓመቱ ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቀዋል።

አክለውም ኮርፖሬሽኑ የተሻለ ትርፋማ እንዲሆን የተለያዩ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት ዋጋ ከማረጋጋት አንጻር በርካታ ተግባራት አከናውኗል።

ኮርፖሬሽኑ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት ከሚመረቱባቸው አካባቢዎች ወደ ተጠቃሚው እያደረሰ መቆየቱንም ገልጸዋል።

በዚህም ባለፈው ስድስት ወር 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚገመት ዋጋ የሚያወጣ የጥራጥሬ ምርት ለሕብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሰራጭ ማድረጉን ነው የተናገሩት።

በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የዳቦ ስንዴ ማሰራጨት መቻሉንም ተናግረዋል።

ይህ ተግባር ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ነው አቶ አቻው የገለጹት።

የዘይት ምርት እጥረትን ለመቅረፍም ኮርፖሬሽኑ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ እና ለህብረተሰቡ እየተከፋፈለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሲሚንቶ ምርትን በተመለከተም በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ከ450 ብር ጀምሮ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ኮርፖሬሽኑ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች በመግዛት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች ማቅረቡን ገልጸዋል።

የኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ በተመረጡ የገበያ ሥፍራዎች እየገባ የዋጋ ግሽበቱ እንዳይባባስ የራሱን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዚህም በበቆሎ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እና በሌሎች የግብርና ምርቶች ላይ የሚታየውን እጥረት ለመቅረፍ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በመርሃግብሩ ወቅት ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ውጤት ለነበራቸው የሥራ ክፍሎች እና ግለሰቦች የገንዘብና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ተሸላሚዎች የተሰጣቸው እውቅና እና የተበረከተላቸው ስጦታ ወደ ፊት ሕዝባቸውን በታማኝነት ለማገልገል እንዲሁም ሥራቸውን በብቃት ለመወጣት ስንቅ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም