ሕብረተሰቡ በገበያ ላይ ያሉ የምግብ ዘይት ምርቶችን አረጋግጦ ሊገዛ ይገባል

81

መጋቢት 09 2014(ኢዜአ) ሕብረተሰቡ በገበያ ላይ ያሉ የምግብ ዘይት ምርቶች ደህንነታቸው የተረጋገጠ መሆኑን አጣርቶ መግዛት እንዳለበት የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አሳሰበ።

በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የምግብ ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር በትረ ጌታሁን፤ ህገወጥ አምራቾች እና ነጋዴዎች  ለጤና ጠንቅ የሆኑ የዘይት ምርቶችን ሊሸጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ሕብረተሰቡ የምግብ ዘይቶችን ሲገዛ ጥራታቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ማጣራት እንዳለበት መክረው ለዚህም በምግብ ዘይት ላይ አስፈላጊ መረጃዎችን  መለጠፋቸውን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።

ከጥራት ማረጋገጫ መንገዶች መካከል መሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች ስለመኖራቸውና የደረጃ ምልክት ስለመለጠፉ ማረጋገጥ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም ሸማቹ የምርት ዘመኑንና የመጠቀሚያ ጊዜውን ማረጋገጥ፣ የአምራቹን ማንነት መለየትና ዘይቱ ከምን እንደተመረተም ማጣራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ባለሥልጣኑ በበኩሉ እውቅና የሌላቸው የምግብ ዘይት ለገበያ እንዳይቀርቡ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ከዚህ ቀደም ባደረገው የገበያ ቅኝትም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ከተከለከሉ የምግብ ምርቶች ውስጥ ዘይት በዋናነት መገኘቱን አስታውሰዋል።

መሰል ድርጊቶች ሊፈጸሙ  ስለሚችሉ ባለሥልጣኑ ክትትሉን እንደሚያጠናክር አመልክተው ባለሥልጣኑ በሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር ያገኘውን ውጤት ለሕዝቡ ይፋ እንደሚያደርግም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚህ ወቅትም በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በሚገኙ 17 ከተሞች ላይ ለሕብረተሰቡ የሚቀርቡ የምግብ ምርት አይነቶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አክለዋል።

መንግስትም የተከሰተውን የምግብ ዘይት እጥረት ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም