የምግብ ግብአቶችን ከአምራቾች በቀጥታ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች ተጠየቀ

61

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 09/2014 (ኢዜአ) በተማሪዎች ምገባ ላይ የሚሰሩ በማኅበር የታቀፉ እናቶች የምግብ ግብዓቶችን ከአምራቾችና ከሸማች ማኅበራት በቀጥታ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችላቸው ጠየቁ።

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በሚገኙ 856 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ628 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመርኃ ግብሩ ተጠቃሚ ሆነዋል።

በተጓዳኝም 800 ሺህ ገደማ ተማሪዎች የትምህርት መረጃ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

በቅርቡም አገልግሎቱን ለማሻሻል ለአንድ ተማሪ የቀን የምገባ ወጪ 16 ብር ላይ 4 ብር እንዲጨምር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ አሳልፏል።

ይህንንም ተከትሎ የምገባ መርኃ ግብሩ በቀን ለአንድ ተማሪ 20 ብር ተመድቦለት ላለፉት አራት ወራት ወደ ሥራ መግባቱን የመዲናዋ የምገባ ኤጀንሲ ገልጿል።

ያም ሆኖ አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር ለአንድ ተማሪ የተመደበው የቀን የምገባ ሂሳብ አይጣጣምም ሲሉ በማኅበር ታቅፈው የሚሰሩ መጋቢ እናቶች ተናግረዋል።

 የተመደበው የቀን የአንድ ተማሪ ወጪ በጀት አነስተኛ በመሆኑና በአንጻሩ ደግሞ የምግብ ግብዓቶች ዋጋ መጨመር ለኪሳራ መዳረጋቸውንም አብራርተዋል።  

በመሆኑም መንግሥት ለአንድ ተማሪ የሚመደበውን በጀት ከፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ጎን ለጎንም የምግብ ግብዓቶችን በቀጥታ ከአምራቾችና ከሸማች ማኅበራት የሚያገኙበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸውም እናቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።

በምገባ መርሃ ግብር ከሚሳተፉ እናቶች መካከል ወይዘሮ ኒኒ መንገሻ በቀን ለምሳ እና ቁርስ 20 ብር እንደሚታሰብላቸው ገልፀው ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ ታሳቢ አለመደረጉ ያነሳሉ፡፡

ፍሬህይወት በቀለ እና ሰላማዊት አስናቀ የተባሉ እናቶች በበኩላቸው ችግሩን ለመቅረፍ መንግስት የምግብ ግብዓቶችን በቀጥታ ከአምራቾችና ከሸማች ማኅበራት የሚያገኙበትን ሁኔታ ቢመቻችላቸው የተሻለ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የምገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አንቺ ነሽ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በምገባ መርኃ ግብሩ ላይ የሚሰሩት እናቶች የገበያ ትስስር ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ኤጀንሲውም ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በማስተሳሰር በቅናሽ ዋጋ የምግብ ግብዓት የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ከፋብሪካ የሚወጡ ምርቶችንም ለመጋቢ እናቶች ለማድረስ ወጣቶችን በማደራጀት አቅርቦቱን ለማሳለጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኤጀንሲው ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ብቻ 85 ሺህ ተማሪዎች የምገባ መርኃግብሩን መቀላቀላቸው ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም