የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል -ርእሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

72

ጋምቤላ መጋቢት 8/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ።

በክልሉ ‘‘የስርዓተ ፆታ እኩልነት ለዘላቂ ልማት’’ በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ሳምንት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው የዓለም የሴቶች ቀን ዛሬ ተጠናቋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ  ኡሞድ ኡጁሉ በወቅቱ እንዳሉት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፓለቲካዊ እድገት ሴቶች ከወንዶች የላቀ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው  ጥናቶች ያመለክታሉ።

ባለፉት ስርዓቶች ለሴቶች ትኩረት በመነፈጉ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስኮች ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው ተገድቦ መቆየቱን  ተናግረዋል።

አሁን ላይ በተጀመረው የለውጥ ምዕራፍ ቁልፍ ጉዳዩች ተብለው ከተለዩ መካከል አንዱ በቤት ውስጥ ብቻ ተገድቦ የነበረውን የሴቶች ሚና በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ጎልቶ እንዲወጣና ያላቸውን ጉልህ ሚና እንዲወጡ ማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግስት ካሳለፋቸው ቁልፍ ውሳኔዎች መካከል የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚልው  እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ክርሚስ ሌሮ በበኩላቸው በክልሉ ተንሰራፍቶ ያለውን "ያለእድሜ ጋብቻ፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ የውርስ ጋብቻና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ሴቶች ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮች እንዲዳረጉ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹን በመከላከልና በማስቀረት ረገድ ሴቶች በተለይም ሴት አመራሮች በግንባር ቀደምትነት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ለሁለት ሳምንት በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ ግንዛቤን በሚፈጥር መልኩ በፓናል ውይይት፣ በኪነ ጥበብና በሌሎች  ዝግጅቶች  ሲከበር የቆየው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዛሬ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም