በከተሞች አረንጓዴ ስፍራዎችን በመገንባት ለኑሮ ምቹ ማድረግና የአየር ፀባይ ለውጥን መከላከል ይገባል -ሚኒስቴሩ

72

ሚዛን፣ መጋቢት 8/2017 (ኢዜአ) በከተሞች አረንጓዴ ስፍራዎችን በብዛት በመገንባት ለኑሮ ተስማሚና ምቹ ከማድረግ ባለፈ የአየር ፀባይ ለውጥን መከላከል እንደሚገባ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስገነዘበ።

ሚኒስቴሩ በከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም የከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ በማተኮር ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራሮች የሰጠው ሥልጠና ተጠናቋል።

በሥልጠናው በክልሉ በፕሮግራሙ የታቀፉ ሦስት ከተሞች ያሉባቸው ተግዳሮቶችን ተነስተው የመፍትሔ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን በሚኒስቴሩ የከተሞች ገቢ ማሻሻያ ፈንድ ሞቢላይዜሽንና ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አምላኩ አዳም ተናግረዋል።

በከተሞች የሚታየው የመልካም አስተዳደርና መሠረተ ልማት ችግሮችን በዕውቀትና በዕቅድ በመምራት መፍታት እንደሚቻል አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል።

በተለይ አረንጓዴ ስፍራዎችን በብዛት ገንብቶ ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ማድረግና የአየር ፀባይ ለውጥን መከላከል እንደሚገባ ኃላፊው አሳስበዋል።

"በከተሞች የሚሰሩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች የአካባቢን ደህንነት ችግር ውስጥ የሚከቱ መሆን እንደሌለባቸው አመልክተው የጎርፍ መፋሰሻ ቦዮች ወደ ወንዞችና ሀይቆች ጎርፍና ሌሎች ፍሳሾች እንዳያስገቡ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል" ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ የማታዓለም ቸኮል እንዳሉት ስልጠናው በክልሉ ከተሞች ያሉትን ጉድለቶችን ለማስተካከል አቅጣጫ እንዳሳየ ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ የሚለቀቀውን በጀት ለህብረተሰብ አገልግሎት በማዋል ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ከተሞች የሚመሩባቸው ዲዛይኖችን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣቸውን ችግሮች የሚቋቋም፣ ለኑሮ ሳቢና ምቹ ከተሞች ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጌታሁን ቢንያም ከስልጠናው ከተማቸውን ተወዳዳሪ ጽዱና ንጹህ ለማድረግ እንዴት መስራት እንዳለባቸው በቂ ግንዛቤ መጨበጣቸውን ገልጸዋል።

"ከመንግስት የምናገኘው ውስን በጀት ላይ ከአጋር ድርጅቶች የምናገኘውን በመጨመር የሚታየውን የመሠረተ ልማት ችግር ለመፍታት ያለመታከት መስራት እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ" ብለዋል።

ለከተማቸው ወሳኝ የሆኑ የውሃ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታና ሌሎችም ማስፋፊያዎችን ከህዝብ ቁጥር ጋር ለማመጣጠን የተያዘውን ዕቅድ ወደ ተግባር ለመለወጥ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

ከተሞች እያስተናገዱ የሚገኙትን ከፍተኛ የሰው ቁጥር በየጊዜው ከመሠረተ ልማትና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ጋር እያስተሳሰሩ መሄድ እንደሚገባ የጠቀሱት ሌላው ተሳታፊ የቦንጋ ከተማ ከንቲባ አቶ ምትኩ ባሹ ናቸው።

''ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከተሞቻችን የተሻለ መነቃቃትና ጤናማ ውድድር ውስጥ ይገኛሉ'' ያሉት አቶ ምትኩ  የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር ሳቢ ገጽታ መገንባት ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

ከስልጠናው ባገኙት ግንዛቤ ከተማውን ለማሳደግ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በሚዛን አማን ከተማ ለሁለት ቀን  በተካሄደው ስልጠና ላይ ከክልሉ የካፋ፣ ሸካና ቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም