የኢንሹራንስና ባንክ የአሰራር መምሪያ ህግ ወቅታዊ አገራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሻሻል ነው

114

መጋቢት 8/2014 (ኢዜአ) የኢንሹራንስና ባንክ የአሰራር መምሪያ ህግ ወቅታዊ አገራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ እየተሻሻለ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የአሰራር መመሪያ ረቂቅ ህጉ በሚሻሻልበት ጉዳይ ላይ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የኢንሹራንስና ባንክ የአሰራር መምሪያ ህግ በ1952 የወጣ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችንና የኢትዮጵያን የኢንሹራንስና ባንክ ዕድገት ታሳቢ ያደረገ ረቂቅ የህግ ማሻሻያ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ ይልቅ ማሻሻያው ከዘመኑ ጋር የማይሄዱና ለአተገባበር ማነቆ የሆኑትን  ህጎች በመለየት ለማሻሻልና የጎደለውን ለመሙላት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ነባሩ ህግ ከወጣበት የዘመን ርቀት በኋላ በርካታ አሰራሮች ሁኔታዎች መለወጣቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም በቀጣይ የውጭ አገር የኢንሹራንስና ባንኮች በኢትዮጵያ እንደሚሰማሩ ታሳቢ በማድረግ የማሻሻያ ረቂቅ ህጉን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡፡

ህጉ ከአገሪቱ ፖሊሲና ህግ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም አሰራር ጋር በተጣጣመ መልኩ በመሻሻል ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

ማሻሻያው የአገር ውስጥና የውጭ የፋይናስ ተቋማትን ልምድ መሰረት አድርጎ የሚዘጋጅ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የሚወጣው ህግ ለረጅም አመታት እንዲያገለግል ታሳቢተደርጎ እንደሚዘጋጅም አስረድተዋል፡፡

በረቂቅ ህጉ ማሻሻያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፣ የዓለም ባንክ ፣ የባንክና የኢንሹራስ ማህበራት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ዩኒቨርስቲዎች ተሳታፊ  መሆናቸው በውይይቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡

ረቂቅ የማሻሻያ ህጉ በስድስት ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም