የምክር ቤት አባላት ሕዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ዋና አፈ ጉባዔዋ አሳሰቡ

69

ሀዋሳ ፤ መጋቢት8/2014 (ኢዜአ) የምክር ቤት አባላት ሕዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በግልጸኝነትና አሳታፊነት አግባብ መወጣት እንዳለባቸው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ አሳሰቡ።

በደቡብ ክልል ለስድስተኛ ዙር ምክር ቤት ተመራጮች በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፣ የፌዴራሊዝምና ፌዴራሊዝም ጽንሰ ሃሳቦች ላይ ያተኮረ ስልጠና በሀዋሳ ከተማ መስጠት ተጀምሯል።

ዋና አፌ ጉባዔዋ በስልጠናው መክፈቻ ወቅት እንዳሉት፤  ምክር ቤቱ በህገ መንግስት የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በተሰጠው ጊዜ በአግባቡ መፈጸምና መጠቀም ይጠበቅበታል።

ለዚህም ከህዝብ የተጣለበትን ሃላፊነት በግልጸኝነትና በአሳታፊነት መንፈስ በማከናወን የህዝብን ፍላጎት ማርካትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአሰራር ስርዓት ማበጀት እንዳስፈለገ አመልክተዋል።

ስልጠናው በምክር ቤቱ ደንብ ቁጥር 16/2008 መሠረት የአሰራር ግልጽነትን በመፍጠር ለህገ መንግስቱና ለመረጠን ህዝብ በታማኝነት ለማገልገል ለገባነው ቃል አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

የምክር ቤት አባላት በስራቸውና በተግባራቸው ክልላዊ እሴቶችን አጎልብተው  የህዝብ ፍላጎት ምላሽ እንዲያገኝ ሃቀኛና ግልጽ በመሆን ሃላፊነታቸውን ለመወጣት  መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የክልሉ ምክር ቤት በቀጣይ አምስት ዓመታት ጉዞ ለማሳካትና የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የአባላቱ የነቃ ተሳተፎ የማይተካ ሚና እንዳለውም አፈ ጉባዔዋ ገልጸዋል።

በስልጠናው በፌዴራል ስርዓት የስልጣን ክፍፍል ውስጥ በፌዴራልና ክልሎች መካከል እንዲሁም በህግ አውጪ ፣አስፈጻሚና ተርጓሚ መካከል ስላለው ሚዛናዊ አሰራር ግንዛቤ ለማሳደግ የሚረዳ ውይይት እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም