ኢዜአ በሀገር ግንባታ ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና አጠናክሮ ይቀጥላል

90

አዳማ፣ መጋቢት 08/2014(ኢዜአ)የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሀገር ግንባታ ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተጋ መሆኑ ተመለከተ።

የተቋሙ 80ኛ አመት ምስረታ በአል በማስመልከት ለሁለት ቀን በአዳማ ከተማ የተካሄደ የፎቶና ቪዲዮ አውደ ርዕይ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢዜአ  የህዝብ ግኑኝነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ወንድይራድ እንደ ገለፁት  አውደ ርዕዩ ኢዜአ ላለፉት 80 አመታት በሀገር ግንባታ ውስጥ የነበረውን ሚና ያሳየና ተቋሙ በቀጣይ ከየት ወደ የት የሚለውን ያመላከተ ነው።

ተቋሙ ከምስረታው ጀምሮ በሀገር ግንባታ ውስጥ የነበረው ሚና የላቀ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል በሚያስችለው ቁመና ላይ ለመድረስ እየተጋ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋሙ በመገናኛ ብዙሀን ዘርፍ በሀገሪቱ ታሪክ ውጤታማ የሆኑ ሙያተኞችን ያፈራ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢዜአ አሁን ላይ የሰው ሀይሉንና አሰራሩን በማዘመን አስተማማኝ የዜና ምንጭነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

በአውደ ርእዩ በርካታ የአዳማ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ፣የምስራቅ ሸዋ ዞንና የአዳማ ከተማ የመንግሥት ሠራተኞችና አመራሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል ።

አውደ ርእዩ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ  ኔትዎርክ ጋር በትብብር የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ አውደ ርእዩን በከፈቱበት ወቅት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ዘመን የማይሽረው ተግባር ማከናወኑን ጠቅሰዋል ።

”ኢዜአ ኢትዮጵያውያን ገንብተዋል ከሚባሉ ተቋማት መካከልም አንደኛው ነው ፤ለዚህም ጊዜና ዘመን የማይሽረው የሕዝብ ተቋም ነው" ማለታቸው ይታወቃል ።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካዊ ከሚባሉ ተቋማት ውስጥ ኢዜአ አንዱ ነው” ሲሉም ገልጸውታል።

ዜና አገልግሎቱ 80ኛ የምስረታ ዓመቱን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት በዋናው መስሪያ ቤቱ ያዘጋጀውን መሰል አውደ ርእይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መጎብኘታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም