ኢትዮጵያ ባከናወነችው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት አገኘች

117
አዲስ አበባ ነሃሴ 28/2010 ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተለያዩ አገራት ጋር ባከናወነችው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ሃብት ማግኘቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሃብቱ ከአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያና ኦሺኒያ አገራት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተገኘ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እያከናወኑት ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ለፖለቲካ ዲፕሎማሲው ስኬት አወንታዊ ሚና መጫወቱ ተገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከየትኛውም አገር ጋር የምትመሰርተው የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚያጠነጥነው በምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ላይ ነው። ይህን እውን ለማድረግም በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ዲፕሎማሲ የሚያጠናክሩ ተግባራት መከናወናቸውን ሚኒስትር ዲኤታው ገልፀዋል። በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጉልህ ተጽዕኖ ከሚኖራቸው አገራት ጋር የተፈጠረውን ግንኙነት ወደ ስትራቴጂክ አጋርነት ማሻገርን ያለሙ ጥናቶች መከናወናቸውንም ለአብነት አንስተዋል። "በቅርብ የደረስንበት ካለው የእድገት ደረጃ ጋር አብረው የሚሄዱት ጥናቶችን እያካሄድን አገራትን መለየት ስለሚገባን በ2010 በጀት ዓመት በርካታ ጥናቶች ተካሄደው ከዘጠኝ የተለያዩ አገራት ጋር ስትራቴጃዊ አጋርነት ደረጃ ሊያደርሱን የሚገቡ ጉዳዮች ተለይተው፤እነዚያ ጉዳዮች ውስጥ የተመለከቱት አንኳር ጉዳዮች ወደ ስራ ተቀይረው ስራዎች እየተሰሩ ነው የሚገኙት። እነዚህም አገሮች አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኩባ፣ ብራዚልና ህንድ ሲሆኑ፤ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለመፍጠር እነዚህ አገራትን መርጠን ጥናቶች አካሄደናል። ከሌሎች አገሮች ደግሞ ከካዛኪስታን ከላቲቪያና ፖላንድ ጋር አጋርነትን ለመፍጠር የሚያበቁ ጥናቶች አካሄደን ወደ ስራ እየገባን ነው የምንገኘው።" በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገሮች ጋር  ያላትን አጋርነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ በርካታ ምክክሮች፣ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባዎችና ስምምነቶች መደረጋቸውንም አውስተዋል። በተለይ ከህንድ፣ ከሩሲያና ቱርክ ጋር የተካሄዱት የጋራ ኮሚሽን ጉባኤዎች ከአገራቱ ጋር ያላትን አጋርነት ማጠናከሩን ሚኒስትር ዲኤታው ጠቅሰዋል። በዓመቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በፕሬዝዳንቱ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ ወደተለያዩ አገራት ጉብኝቶች ተደርገዋል። እነዚህና መሰል የዲፕሎማሲ ክንዋኔዎችም አገሪቱ ለተለያዩ የልማት ስራዎች የሚውል ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንድታገኝ አስችሏታል። "ጃፓን ለብዙ ዓመታት አቋርጣ የነበረውን የብድር አቅርቦት ማቅረብ ችላለች። ህንድና ቻይናም አጠናክረው የልማት ትብብርና ድጋፍ ስራዎችን መቀጠል ችለዋል። በተለይ ጀርመን በመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት አቋርጣው የነበረውን ትብብር እንዲቀጥል ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተሰርተው ያን መቀጠል ተችሏል። ከዩናይትድ ስተቴት ከእንግሊዝ እና ከሌሎች መልቲ ላተራል ፋይናንስ ተቋማት የሚደረግልን ትብብር እንዳይስተጓጎል ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ ተሰርቶ ከእነዚህም ሶስት አህጉራትና ከተወሰኑ የመልቲ ላተራል ድርጅቶች ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ለተያዩ አገራዊ የልማት ሰራዎች እንዲሆን ማድረግ የተቻለበት ዓመት ነው።" በተለያዩ አገራት የኢትዮጵያን ውክልና ለማስፋት በበጀት ዓመቱ በተወሰዱት እርምጃዎች በአውሮፓና አሜሪካ የተለያዩ የክብር ቆንስላዎች መሰየም መቻሉን አውስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተለያዩ አገራት ጋር እያከናወኑት ያለው ግንኙነት ለአገሪቱ የፖለቲካ ዲፕሎማሲ የስኬት በር እየከፈተ መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታው አክለዋል። "ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ወደ ጎረቤት ሃገራት ሄደው ነው የኢትዮጵያን የልማትና የእድገት አቅጣጫ ከመሪዎች ጋር ተነጋግረዋል፤ ከዚያም ቀጥሎ ወደ መካከለኛው ምሰራቅ  ከዚያም የአገራችን ዜጎች በርከት ብለው ወደሚገኙበት  አሜሪካን ጎብኝተው ከወገኖቻችን ጋር ተመካክረው አጋጣሚውን በመጠቀም ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር በመገናኘት ሰፊ ስራ ሰርተው ነው የመጡት።በአጠቃላይ ሰብሰብ ሲደረግ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የከፈቷቸው በርካታ በሮች ለፖለቲካ ዲፕሎማሲ ስራችን ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ነበር።" የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ ጥሎት የነበረው ማዕቀብ እንዲነሳ ኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗንም አስታውሰው፤ በቀጣይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በማዳበር ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር እንዲፈጠር ትሰራለች ብለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም