በክልሉ የጸጥታ መዋቅሩን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጀሉ

64

ጋምቤላ፤ መጋቢት 7/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የጸጥታ መዋቅሩን ይበልጥ በማጠናከር ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጀሉ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፤ የውስጥና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በመከላከል በክልሉ አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የብልጽግናውን ጉዞ የማፋጠኑ ሂደት ለማስቀጠል እየተሰራ ነው።

ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ብሎ የሚጠራው  የሸኔ የሽብር ቡድን ተላላኪና የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ታጣቂዎች የክልሉን ሰላም ለማወክ የሚያደርጉትን ሙከራ በዘላቂነት ለማስቀረትም እንዲሁ።

በተለይም  የሙርሌ ታጣቂዎች በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች እየፈጸሙ ያሉትን ህፃናትን አፍኖ የመውሰድና የቀንድ ከብት ዘረፋ ወንጀል ለመከላከል በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮችን በሰው ኃይልና በግብዓት በማጠናከር በክልሉ ሰላምና ልማትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊው በበኩላቸው፤  የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ታጣቂዎች ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በአኝዋሃና በኑዌር ዞኖች ተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርሱ መቆየታቸውን  ተናግረዋል።

የሙርሌ ታጣቂዎች ባለፉት ዓመታት የሰዎችን ህይወት በማጥፋት  በርካታ ህፃናትን አፍነው ከመውሰዳቸውም በተጨማሪ ከአምስት ሺህ በላይ የቀንድ ከብቶችን መዝረፋቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንን ችግር ለማስቀረት የጸጥታ መዋቅሩን የማጠናከሩ ተግባር አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን  ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው አስተማማኝ ሰላም መገንባት ሲቻል ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ፖሊስ  ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ ናቸው።

ኮሚሽኑ ከህዝቡ ጋር በመሆን የክልሉን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም