የአማራ ልማት ማህበር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዙ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው

72

ጎንደር፤ መጋቢት 7/2014(ኢዜአ) የአማራ ልማት ማህበር /አልማ/ ከ176 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዙ የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ማህበሩ የሀብት አሰባሰብ አፈጻጸሙን ለማሻሻል የሚያግዝ የህዝብ ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ አካሂዷል፡፡

በልማት ማህበሩ የጎንደርና አካባቢው አልማ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለኸኝ ጓዴ እንደተናገሩት የልማት ፕሮጀክቶቹ እየተካሄዱ የሚገኙት ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ነው፡፡

በዚህም ዘንድሮ   ግንባታቸው የተጀመሩት የልማት ፕሮጀክቶች  በ85 ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሆነና  ከ165 ሺ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከግንባታዎቹ መካከልም ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-መጻሀፍቶችና ቤተ-ሙከራዎች ይገኙበታል፡፡

በቀጣዩ ዓመት መስከረም ወር ውስጥ   ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፈው ዓመት  በ56 ሚሊዮን ብር ወጭ የተጀመሩ 10 የልማት ፕሮጀክቶችም በተያዘው ዓመት  መጨረሻ እንደሚጠናቀቁ አስረድተዋል፡፡

''ማህበሩ የልማት ፕሮጀክቶቹን የሚያከናውነው ከህዝብ በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው'' ያሉት ሃላፊው እስካሁንም ህዝቡ 60 ሚሊዮን ብር የገንዘብ መዋጮ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

''አልማ ለክልላችን ህዝብ በርካታ የልማት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል'' ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይ ናቸው፡፡

ማህበሩ የለውጥ ዕቅድ አዘጋጅቶ በትምህርት ዘርፍ በተለይም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሳደግ ረገድ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ እያከናወናቸው የሚገኙትን  የትምህርት ስራዎችን በእቅዱ መስረት ማሳካት እንዲቻል ከማህበሩ አባላትና ከለጋሽ ድርጅቶች ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የጎንደር ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ እንዳሉት፤ በከተማው 76 የግልና የመንግስት የትምህርት ተቋማትን ደረጃ በማሳደግ ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ለመፍጠር እየተስራ ነው።

ማህበሩ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እያበረከተ ያለውን የልማት ድጋፍ ለማጠናከር ህብረተሰቡ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል የተማሪ ወላጅ ህብረት ፕሬዚዳንት አቶ አዱኛ እሽቴ በበኩላቸው፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ ተግባር እንዲሳካ ማህበሩ የጀመረውን ጥረት በሚቻለን አቅም ሁሉ እንደግፋለን ብለዋል።

የአማራ ልማት ማህበር/ አልማ/ በ1983 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 4 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ አባላት እንዳሉትም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም