ኢዜአ በኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ዘመን የማይሽረው ተግባር ሲያከናውን የቆየ ተቋም ነው

89

መጋቢት 7/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኢትዮጵያ ግንባታ ሂደት ዘመን የማይሽረው ተግባር ማከናወኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ፡፡

ኢዜአ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦ.ቢ.ኤን) ጋር በመተባበር በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው የፎቶ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።

በዚሁ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካዊ ከሚባሉ ተቋማት ውስጥ ኢዜአ አንዱ ነው።

ይህ ብቻ ሳይሆን ''ኢዜአ ኢትዮጵያን ገንብተዋል ከሚባሉ ተቋማት መካከልም አንደኛው ነው'' ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም ጊዜና ዘመን የማይሽረው የሕዝብ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።      

ኢትዮጵያ እዚህ የደረሰችው ታሪክ እየተጻፈ፣ መረጃ እየተደራጀ፣ ተቋማት እየተመሰረቱ በትውልድ ቅብብሎሽ ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደትም የኢዜአ ሚና ከፍተኛና ዘመን የማይሽረው እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢዜአ በተለይም ከኦ.ቢ.ኤን ጋር በመሆን የኢትዮጵያውያን የለውጥ ፍላጎት ፍሬ እንዲያፈራ ብዙ ስራ ሰርተዋል ብለዋል ዶክተር ቢቂላ።

ሁለቱ ሚዲያዎች ባለፉት አራት ዓመታት የታዩ ስኬቶችን በመዘገብና ለህዝቡ ግንዛቤ በመስጠት ረገድ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ እንደነበርም ጠቁመዋል።

ተቋማቱ ወደ ፊትም ኢትዮጵያውያንን የሚያቀራርቡ ተግባራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ሲሆን እኩይ ዓላማ ይዘው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መከላከል ይቻላል ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ።

በአውደ ርዕይው ላይ የተሳተፉ እንግዶች በሰጡት አስተያየትም ኢዜአ ረጅም ዓመታትን በስኬት የዘለቀና ለወደፊትም በርካታ ስራዎች የሚጠብቁት ተቋም ነው ብለዋል።

ኢዜአ በርካታ የዘገባ ስራዎች በአዳማ ከተማ ላይ እንደሚሰራም ጠቁመው፣ ለወደፊትም ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ይህ አውደርዕይ ማሳያ ነውም ብለዋል።

በአዳማ ከተማ በተከፈተው የፎቶ አውደ ርዕይ ላይ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ አባገዳዎች፣ ኢዜአ እና የኦ.ቢ.ኤን ከፍተኛ ስራ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ግለሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም