ፓርቲው በጉባኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ለመተግበር በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል

88

መጋቢት 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ በጉባኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ለመተግበር በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።

ተቋሙ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤን መነሻ በማድረግ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ፤ፓርቲው ባካሄደው አንደኛ ጉባኤ ትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ማሳለፉን ጠቅሷል።

ፓርቲው የህግ የበላይነትን ለማስከበር፣ የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል፣ በሶማሌና ኦሮሚያ እንዲሁም በደቡብ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል ውሳኔ ማሳለፉ ተገቢ መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በአፋር፣ ትግራይ፣ በአማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በሌሎችም አካባቢዎች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል።

የድርቅ ተጎጂ ዜጎችን ለመታደግም በቂ የእለት ደራሽ ምግብ ማቅረብና የእንስሳት መኖና ውኃ ማቅረብ እንደሚገባም አሳስቧል።

በዚህ ዙሪያ ለሕዝቡ በቂ መረጃ እንዲሰጥ በማስገንዘብ የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታት አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚው የሚመራበት ግልጽ ፖሊሲ ማስቀመጥና ለግብርናው ዘርፍ ተገቢ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብሏል ተቋሙ በመግለጫው።

የንግድ ስርዓቱ ከአሻጥርና ከህገ-ወጥነት እንዲላቀቅ መንግስት አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድም አሳስቧል።

እነዚህ ጉዳዮች ትኩረት ካገኙ ባለፉት ዓመታት ተከስተው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ነው ያነሳው።

በጥቅሉ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና፣ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል ግልጽ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተነድፈው እንዲተገበሩ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ብልጽግና ፓርቲ ያካሄደው ጉባኤ በመሳካቱ ''እንኳን ደስ አላችሁ'' ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም