ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ካሳወቃቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እስካሁን ጉባኤያቸውን ያካሄዱት አራት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው

79

መጋቢት 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄዱ ካሳወቃቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እስካሁን ጉባኤያቸውን ያካሄዱት አራት ፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን ቦርዱ አስታወቀ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄዱ የተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱና የሰነድ ማሻሻያ እንዲያደርጉ የተገለጸላቸው 26 አገራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን አጠናቀው ባለማቅረባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ እና ለቦርዱ እንዲያስገቡ መግለጹ ይታወሳል።

ከ26ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ያካሄዱት አራት ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን ኢዜአ ከምርጫ ቦርድ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ብልጽግና ፓርቲ፣ የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ(ጋሕነን)፣ሕዳሴ ፓርቲና ከፋ አረንጓዴ ፓርቲ ጉባኤያቸውን ያካሄዱ ፓርቲዎች ናቸው።

ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ የሚካሄድበት የጊዜ ገደብ እንዲራዘምላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ ሉዓላዊነትና የአፋር ሕዝቦች ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ “በጸጥታና ስብስባ ማካሄጃ ቦታ ማጣት ጉዳዮች ምክንያት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ማካሄድ አንችልም” በሚል ያቀረቡት የይራዘምልን ጥያቄ ምርጫ ቦርድ አሳማኝ ሆኖ ስላገኘው እንዳራዘመላቸው ገልጿል።

ቀሪዎቹ የጠቅላላ ጉባኤ ይራዘምልን በሚል ጥያቄ ያቀረቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ባደረጉት ውይይት መሰረት በቂ ማስረጃና ጉባኤ የሚያካሄዱበትን ቀን ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ጥሪ ቀርቧል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ 

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም