ቆላማ አካባቢዎችን በማልማት የድርቅ ተፅዕኖን ለመቋቋም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ ያስፈልጋል

236

አዳማ ፤ መጋቢት 07/2014( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎችን በማልማት ድርቅ እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስቴርና የጀርመን ተራድኦ ድርጅት በኮሮና ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን በሀገሪቱ  ቆላማ አካባቢዎች በትብብር ለማልማት የነበረውን እንቅስቃሴ አሁን በአዲስ መልክ ማስቀጠል  በሚቻልበት ላይ በአዳማ ከተማ ምክክር እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ  እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ማልማት የድርቅ  ተፅዕኖ በዘላቂነት ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የላቀ ድርሻ አለው።

ድርቅና ተለዋዋጭ የአየር ሁኔታ ተደጋጋሚ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለመደው አሰራርና አካሄድ አካባቢውን ማልማትም ሆነ መለወጥ አንችልም ብለዋል።

መንግስት አዳዲስ አሰራሮች፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀርፆ ወደ ተግባር መግባቱን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው፤  ከ400ሺህ ሄክታር ላይ እየለማ ያለው የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት አንዱ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

በልገሳ  ብቻ  ችግሩን መፍታት ስለማያስችል ለድርቅ ተፅዕኖ ቅነሳ፣ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና ለቆላማ አካባቢ ልማት አዳዲስ አሰራር እየዘረጋን ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በቆላማ አካባቢዎች የመስኖ ግድቦች ግንባታ በስፋት ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል ።

በቆላማ አካባቢዎች በቀጣይ 10  ዓመት ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ ፣  የቆላ ጥራጥሬና የሸንኮራ አገዳ ለማልማት መታቀዱንም ጠቁመዋል።

ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎችን በማልማት  የድርቅ ተፅዕኖን ለመቋቋም የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ  ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስታወቁት።

በሮም የኢትዮጵያ የልማትና ሰብዓዊ መብት ድጋፍ አስተባባሪ ዶክተር ካባ ዑርጌሳ በቪዲዮ ኮንፈረንስ በሰጡት መግለጫ ፤ በኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ያሉት ተግዳሮቶች ለማቃለልና ልማቱን ለማቀላጠፍ  በትብብር መስራት ይገባናል ብለዋል።

የምግብ፣ የእንስሳት መኖ፣ ምርጥ ዘርና የእንስሳት እርባታ በአካባቢው በሰፊው ማልማት እንችላለን፤ ለዚህም የጋራ ዕቅድ፣ትብብርና ቅንጅት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የጀርመን ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ኤልዛቤት ቫንዴንአከር እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎችን ለማልማት የጋራ ትብብር፣ ቅንጅትና አቅም ግንባታ ወሳኝ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ቆላማ አካባቢዎችን ለማልማት ያዘጋጀው  የ10  ዓመት ዕቅድ  ውጤታማ እንዲሆን የጋራ ትብብር፣ ቅንጅትና የማስፈፀም አቅም ማጎልበት አለብን ብለዋል።

ድርቅና የምግብ እጥረት ችግሮችን ለማቃለል ጭምር በጋራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

መድረኩ ለቀጣይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የአርብቶ አደሮች ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።