በእስራኤል አገር የልብ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ልጆቻችን እድሉን በማግኘታቸው ጭንቀታችን ተቃሏል

164

አዲስ አበባ  መጋቢት 6/2014 /ኢዜአ/ በእስራኤል አገር የልብ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ልጆቻችን እድሉን በማግኘታቸው ጭንቀታችን ተቃሏል ሲሉ የህጻናቱ ወላጆች ገለጹ።

በእስራኤል የልብ ቀዶ ህክምና ለማድረግ  11 ህጻናት ወደ እስራኤል ቴላቪቭ ተሸኝተዋል።

ለህጻናቱ ህክምናውን ያመቻቸው በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ "ሴቭ ዘ ቻይልድ ኸርት" ከተሰኘው ድርጅት ጋር በመተባበር ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ህጻናቱን ሸኝተዋል።            

እድሉን ካገኙት የህጻናት ቤተሰቦች መካከል ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ሻኪራ ሙዘየር  አንዷ ናቸው።        

ህጻን ልጃቸው ከሦስት ወር እድሜዋ ጀምሮ መታመሟን የሚናገሩት ወይዘሮ ሻኪራ ሙዘየር፤ "ልጄን ለማሳከም በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፌያለሁ" ይላሉ።    

"ያን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፌ ዛሬ ልጄ ወደ እስራኤል አገር ሄዳ የመታከም እድል በማግኘቷ እጅግ ተደስቻለሁ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡                

የስምንት ወር ልጃቸው በተወለደ በ22 ቀኑ የልብ ህመም እንዳለበት እንደተነገራቸው የሚገልጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፌቨን አበበ ናቸው።

የልጄን ህመም ቃላት አይገልጸውም ያሉት ወይዘሮ ፌቨን፤ ያገኙት እድል ለጭንቀታቸው ምላሽ የሰጠ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡    

የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አዲስዓለም ታደሰ፤ የሰባት ወር እድሜ ያላት ልጃቸው የልብ ህመም እንዳለባት የታወቀው በተወለደች በስምንተኛ ቀኗ መሆኑን ይናገራሉ፡፡   

"በግል ለማሳከም አቅም የለንም፤ ይሄ ለእኛ ትልቅ እድል ነው፤ መሰል ችግር ላለባቸው ሌሎች ህጻናትም እድሉ ሊመቻች ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።  

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ በበኩላቸው፤ እስራኤል ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራት የሚኖሩ የልብ ህሙማን ህጻናት ህክምና እንዲያገኙ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።  

በተለይም "ሴቭ ዘ ቻይልድ ኸርት" ከተሰኘው ድርጅት ጋር በመተባበር በአፍሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በእስራኤል ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰዋል።  

በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት 772 ህጻናት ህክምናውን አግኝተው ወደ ሙሉ ጤንነት መመለሳቸውን ተናግረዋል።   

አንድን ህጻን በውጭ አገር ለማሳከም በነፍስ ወከፍ እስከ 20 ሺህ ዶላር እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የእስራኤል መንግስት ህክምናው በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲጠናከር እገዛ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ወደ እስራኤል አቅንተው እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እስራኤል ያሉ የልብ ህክምና ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ህክምና እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ ቀደም የእስራኤል ባለሙያዎች በኢትዮጵያ በሦስት ዙር የህክምና አገልግሎት መስጠታቸውን ገልጸዋል።     

እስራኤል በቀጣይ ለኢትዮጵያ በዘርፉ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም