ብልጽግና በኢትዮጵያ የነበረውን የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህል በማስቀረት ተራማጅ አስተሳሰብ ይዞ የመጣ ፓርቲ ነው - አቶ ደመቀ መኮንን

101

መጋቢት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) ብልጽግና በኢትዮጵያ የነበረውን የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህል በማስቀረት ተራማጅ አስተሳሰብ ይዞ የመጣ ፓርቲ መሆኑን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ፓርቲው አንደኛ ጉባኤውን በስኬት ማካሄዱን አስመልክቶ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ደመቀ መኮንን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ህብረብሔራዊ አንድነቷን የጠበቀች ጠንካራ አገር ለመገንባት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው በመግለጫቸው የጠቆሙት፡፡

ብልጽግና የመሪነት ሚናውን መወጣት ሲጀምር ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታትና መጪውን ዘመን የተሻለ ለማድረግ ዓላማ ሰንቆ ነው ብለዋል፡፡

ቀድሞ በተግባር ተጀምረው የነበሩ የለውጥ ሂደቶች በጉባኤው ጥልቀት እንዲያገኙ እና ጉባኤው የበለጠ ግንዛቤ ይዞ ለተፈጻሚነታቸው ይበልጥ እንዲንቀሳቀስ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

እንደ አገር ለውጡ ለአራት ዓመት ሲመራም ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ እና ግልጽ የሆነ መዳረሻ ተይዞ እንደነበርም ነው የጠቆሙት፡፡

በለውጡ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

በጉባኤውም የነበሩበትን ክፍተቶች በማረም የታዩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ረገድ የተለያዩ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ጠቁመዋል፡፡

ፓርቲው ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ፈታናዎች እንደገጠሙት አስታውሰው፤ በዋናነትም የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህል ትልቅ ፈተና እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የገጠሙ ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች መካከል ሌብነት፣ ድርቅና መሰል ጉዳዮችን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥላቻዎችና ለዓመታት እየተንከባለሉ የመጡ ስር የሰደዱ ችግሮች እንደነበሩም ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በችግሮች መካከል ሆኖ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶችን ማስመዝገቡንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዓመታትን ያስቆጠረውን ኢህአዴግን ውህድ ፓርቲ የማድረግ እንቅስቃሴ በብልጽግና ዘመን እውን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከልማት ፕሮግራሞች አኳያም ስኳር ፋብሪካዎች እውን ሆነዋል፤ ሜቴክ ላይ የነበሩ ችግሮች እንዲፈቱ ተደርገዋል ብለዋል አቶ ደመቀ፡፡

"ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ጌጣችን ነው" ያሉት አቶ ደመቀ፤ መዳረሻችን ጠንካራ አገር መገንባት እና የዜጎችን ህይወት ማሻሻል ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም