ቤተ ዕምነቶች ትውልዱን በግብረ ገብነትና በሞራል የማነጽ ስራቸውን በትኩረት ሊሰሩ ይገባል

134

አዲስ አበባ መጋቢት7/2014 /ኢዜአ/ ቤተ ዕምነቶች ትውልዱን በግብረ ገብነትና የማነጽ ስራቸውን በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በመዲናዋ ለሚያስገነባው ህንጻ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ በኢትዮጵያ ሰላምና መከባበር እንዲኖር የቤተ ዕምነቶች ሚና የላቀ ነው ብለዋል።

ለተግባራዊነቱ ትውልድን በግብረ ገብነት  ለማነጽ  ቤተ ዕምነቶች በተለየ ሁኔታ መሥራት አለባቸው ይላሉ።

መንግሥት የተሻለች አገር እንድትኖር ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ቤተ እምነቶች ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪም አቅርበዋል።

እንደ ከንቲባዋ ገለጻ ከተማ አስተዳደሩም የቤተ ዕምነቶችን ጥያቄ በእኩልነት ለመመለስ እየሰራ ነው።

ለዚህ ደግሞ ካውንስሉ ለሚያሰራው ህንጻ መንግስት መሬት ማቅረቡ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዘዳንት ዶክተር ጣሰው ገብሬ በበኩላቸው መስተዳደሩ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

የህንጻው መታሰቢያነትም በኢትዮጵያ ምድር ወንጌልን በማስተማር ዋጋ ለከፈሉ ቀደምት የቤተክርስቲያን  አባቶች እንደሆነ ገልፀዋል።

ካውንስሉም ከመንፈሳዊ አገልጋሎቷ ባሻገር በሰላም እሴት ግንባታ ላይ በስፋት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

ፕሬዚዳንቱ በህንፃ ግንባታው ላይ ሁሉም አሻራውን እንዲያሳርፍም ጥሪ አቅርበዋል።

ህንጻው በ10 ሺህ 400 ካሬ ሜትር መሬት ላይ የሚገነባ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም