አሁን እየታየ ያለው ሙቀት በበልግ ወቅት የሚጠበቅ የአየር ሁኔታ ነው-የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት

129

መጋቢት 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሁን እየታየ ያለው ሙቀት በበልግ ወቅት የሚጠበቅ የአየር ሁኔታ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

የበልግ ዝናብ ከጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ እንደሚጀምር ገልጿል።

የበልግ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚመዘገብበት መሆኑንና አሁን እየተስተዋለ ያለው ነገር ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመዲን አብዱልከሪም ለኢዜአ ገልጸዋል።

የበልግ ወቅት የዝናብ ተጠቃሚዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች ዝናብ እንደሚኖርና በሙቀቱ ምክንያት በውሃ አካላትና ግድቦች ላይ ያለው የትነት መጠን እንደሚጨምር ኢኒስቲትዩቱ የበልግ ወቅት ትንበያውን ይፋ ባደረገበት ወቅት ማሳወቁን ተናግረዋል።

በበልግ ወቅት እየታየ ያለው የዝናብ ስርጭት በአመዛኙ ከመደበኛ በታች እንደሆነና የተወሰነ ዝናብ ዘንቦ በአብዛኛው ደረቃማ የአየር ጸባይ እየተስተዋለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት ትንበያ መሰረት ከጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ ደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች የበልግ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ከበልግ ዝናብ ሽፋን አኳያ አብዛኛው የምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የበልግ ዝናብ ያገኛሉ ብለዋል።

የበልግ ወራት ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የሰሜን ምስራቅና መካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል እንዲሁም የደቡብ ከፍተኛ ቦታዎችና ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በታች የበልግ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉም አብራርተዋል።

ከጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በበልግ ዝናብ ተጠቃሚዎች የደመና ክምችቱ እየተጠናከረ በመምጣት መጠነኛ እርጥበት ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዳይሬክተሩ አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ እርጥበቱን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ገልጸዋል።

በበልግ ወቅት ከመደበኛው በታች ዝናብ የሚያመዘን በመሆኑ በውሃ አካላትና በግድቦች ያለውን ውሃ በአግባቡ መጠቀምና በአጠቃላይ ውሃን በጥንቃቄ መያዝና ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ አቶ አህመዲን አሳስበዋል።በኢትዮጵያ የበልግ ወቅት የሚባለው ከየካቲት እስከ ግንቦት ወር ያለው ጊዜ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም