ፓርቲው በጉባኤው ላሳለፋቸው ውሳኔዎች ተፈፃሚነት የኀብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና አለው

58

አዲስ አበባ  መጋቢት  5/2014 /ኢዜአ/ ብልጽግና ፓርቲ በጉባኤው ላሳለፋቸው ውሳኔዎችና ላስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ተፈፃሚነት የኀብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ለሦሰት ቀናት የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና ያረጋግጣሉ  ያላቸውን ውሳኔዎች በማሳለፍ ተጠናቋል።

ጉባኤው አገራዊ ለውጡን ማስቀጠል፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር፣ የአገርን አንድነትና የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ፣ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅና ሌሎች ነጥቦችን ያካተተ የአቋም መግለጫ በማውጣት ነው የተጠናቀቀው፡፡

ኢዜአ በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ዳግማዊ ገነነ ና አቶ አየለ አባቡሌ እነዚህን መሰረታዊ ጉዳዮች ወደ መሬት በማውረድ ተግባራዊ ለማድረግ የፓርቲው አመራርና አባላት፣ ደጋፊዎችና አጠቃላይ ህዝቡ የጋራ ጥርት ማድረግ አለበት ብለዋል።

የፓርቲው ውሳኔዎች ቢተገበሩ ለአገር፣ ለህዝብና መንግስት ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ስላላቸው ለተግባራዊነታቸው መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በአገር ጉዳይ የመልካም ነገሮች ተጋሪ፤ የችግሮች ተካፋይ የምንሆነው ሁላችንም ለአገራችን ሰላምና ልማት ልዩ ትኩረት መስጠት ስንችል ነው ብለዋል፡፡

ፓርቲው የአገር ልማትና የህዝብን ጥቅም ለማስከበር ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ያለ ህብረተሰቡ ድጋፍ በውጤታማነት ሊተገበሩ እንደማይችሉም አስተያየት ሰጪዎቹ አቶ መላክ ጌታነህ ና አቶ ጣሰው በሪ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡

ፓርቲው በተለይ በህብረተሰቡ ዘንድ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን ጉዳዮች በአፋጣኝ ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ፓርቲው ያሳለፋቸውን  ውሳኔዎች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በማውረድ ለተግባራዊነታቸው መስራት እንዳለበትም ነዋሪዎቹ  አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም