የኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያላከበረና የአገርን ጥቅም የሚጎዳ ነው

64

መጋቢት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያላከበረና የአገርን ጥቅም የሚጎዳ ነው”ሲሉ በአሜሪካ ቦስተን የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደረጀ ደምሴ ገለጹ።

በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ)፣ ያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

በአሜሪካ ቦስተን የሕግ ባለሙያ አቶ ደረጀ ደምሴ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት “ኤችአር 6600" ረቂቅ ሕግ በኢኮኖሚ፣በወታደራዊ፣በሕግ አካሄድና የንግግር ይዘቶችን መገደብ ላይ ትኩረት አድርጓል።

በኢኮኖሚው መስክ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ እንዳታደርግና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ ብድርና እርዳታ እንዳይሰጡ ጫና እንደሚያሳድርም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ መደበኛ የጦር መሳሪያዎችን ከነመለዋወጫዎቻቸው እንዳትገዛ ክልከላ ማድረግና መሳሪያውን የሚሸጡ አገራትና ባለስልጣናት በሕግ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው እንደሚገልጽም አመልክተዋል።

ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች ለሕግ ካልቀረቡ ኢትዮጵያ ከአሜሪካና ከሌሎች አገራት የምታገኛቸው እርዳታዎችና ድጋፎች መቆም አለባቸው የሚል ሀሳብ መያዙን ጠቅሰዋል።

ሕጉ ከጸደቀ ከአሜሪካ ውጪ የሚኖሩና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚናገሩ ሰዎች መልዕክቶቻቸው በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዳይተላለፉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ረቂቅ ህጉ በአሜሪካ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከተዘጋጁ ረቂቅ ሕጎች መካከል ኢትዮጵያን በእጅጉ የሚጎዳና ሉዓላዊነቷን የማያከብር መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ረቂቅ ሕጉ “በኢትዮጵያ ሰላም፣ዴሞክራሲና መረጋጋት ማምጣት” የሚል ስያሜ ያለው ቢሆንም በውስጡ የያዛቸው ሀሳቦች በተቃራኒው ኢትዮጵያን የሚጎዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአሜሪካ መንግስት ተቋማት ከተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው በኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደር ዓላማ ያለው መሆኑን አመልክተዋል።

ሕጉ ከጸደቀ ለ10 ዓመት የሚያገለግል በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ቀጣይነት ያለው ጫና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

‘ኤችአር 6600’ በኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ሊቃወሙት ይገባል ብለዋል።

ረቂቅ ሕጉ የአሜሪካ መንግስት ፍላጎት ሳይሆን የተወሰኑ የአሜሪካ ባለስልጣናት ኢትዮጵያን ለመጉዳት ያዘጋጁት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ረቂቅ ሕጉ የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ተወያይቶበት ሙሉ ኮንግረሱ እንዲወያይበት መመራቱን አመልክተዋል።

ረቂቅ ሕጉን ለማጸደቅ በአሜሪካ ኮንግረስና ሴኔት ባሉ የሕግ ሂደቶች ውስጥ እንዲወድቅ ወይም ደካማ እንዲሆን ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ  የተቀናጀ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።

የዳያስፖራ አባላት ረቂቅ ሕጉን በሚገባ ተረድተው በየአካባቢያቸው ላሉ ተመራጮች ማስረዳት፣ደብዳቤ መጻፍና በስልክ ማነጋገር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ በአሜሪካ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የዳያስፖራ ተቋማት ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ዳያስፖራው የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዱ የአሜሪካ ባለስልጣናትን እ.አ.አ በ2022 የግማሽ ዓመት ምርጫ በድምጹ መቅጣት እንደሚገባውም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማስረዳት በተለይም የሰብዓዊ ድጋፍን አስመልክቶ ያሉ ጉዳዮች ላይ ለአሜሪካ መንግስት ማብራሪያ ቢሰጥ የረቂቅ ሕጉን የመጽደቅ እድል እንደሚያጠበውም ተናግረዋል።

መንግስት ሰላምን ለማምጣት እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶችና እየገጠሙት ያሉ ችግሮችን አስመልክቶ ገለጻ ማድረግ እንደሚገባውም አብራርተዋል።

የኢትዮ-አሜሪካውያን የእድገት ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት፣ ’አሜሪካን ኢትዮጵያንስ ፐብሊክ አፊርስ ኮሚቴ፣ የ”በቃ” ወይም #NoMore ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴና ሌሎች የሲቪክ ተቋማት የ ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ዘመቻ እያደረጉ እንደሚገኙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም