የመዲናዋ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት የእንግልትና የህገ ወጦች መንስኤ ሆኗል

78

መጋቢት 05 ቀን 2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ፣ እንግልቱና የህገ ወጦች መበራከት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተገልጋዮች ገለጹ።

የከተማ አስተዳደሩ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በበኩሉ አገልገሎቱ በኔትወርክ መሰረተ ልማት ችግር ሳቢያ እንከን ገጥሞታል ብሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ለማውጣትና ለማደስ እንዲሁም የልደት፣ የሞትና የጋብቻ ሰርተፍኬት ለማግኘት ችግሮች መኖራቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ቅኝት ባደረገባቸው አካባቢዎች አረጋግጧል።

ሪፖርተራችን በቅኝት ካረጋገጠባቸው ማእከላት መካከል በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አገልግሎት ለማግኘት አረጋዊያን፣ ሴቶች እንዲሁም ወጣቶች በረጀም ሰልፍና በትርምስ ውስጥ ቢጠባበቁም አገልገሎት መስጠቱ እንኳን ቀርቶ ቀና ምላሽ የሚሰጥ የቢሮ ሰው ወይም ሃላፊ የለም ሲሉ ያማርራሉ።

በወረዳው የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ችግር ቀደም ሲል ቢኖርም አሁን ላይ ግን ይበልጥ እየተወሳሰበ ላልተገባ ወጪ፣ እንግልትና ምልልስ ዳርጎናል ሲሉ ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

በወረዳው አገልግሎት ፈልጎ ከሚሰለፈው በተጓዳኝ "ጉዳይ እናስፈፅማለን" የሚሉ ህገ ወጦች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የአገልገሎት ማግኛ ሳይሆን ከፍተኛ የእንግልት ስፍራ ሆኗል ይላሉ።

መታወቂያ ወይም የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ጉዳይ "አገልጋይ የሌለበት፣ ለህገ ወጥ ደላሎች ገበያ፤ ለተገልጋዮች ደግሞ የእንግልትና ምሬት ምክንያት ሆኖ ቀጥሏል" ብለዋል።

በአዲስ አበባ የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ጠጅቱ ደገፋ፤ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ላይ የተፈጠረው ችግር ከወረዳው አቅም በላይ ሆኗል ይላሉ።

በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ወቅታዊ  ሁኔታ ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላው አገሪቱ ከጥቅምት 23/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆንና ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጁን በማስታወስ አዲስ የመኖሪያ መታወቂያ መስጠት አዋጁ ከደነገጋቸው ክልከላዎች መካከል መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም በአዋጁ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው አገልግሎት ከየካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎች አገልገሎቱን ለመስጠት ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ሆኖም አገልግሎቱ የሚሰጥበት ቴክኖሎጂ የኔትወርከ መጨናነቅ የሚስተዋልበት በመሆኑ በሚፈለገው መጠንና ፍጥነት አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለና የከተማ አስተዳደሩ የችግሩን አሳሳቢነት በአግባቡ ተገንዝቦ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በበኩሉ በአገልገሎት መስጫ ቴክኖሎጂው ላይ የኔትወርክ መሰረተ ልማት መቋረጥ በማጋጠሙ ችግሩ ተከስቷል ብሏል።

የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር መላከ መኮንን፤ በስልክ በሰጡን ምላሽ የወሳኝ ኩነት አገልግሎት ቀደም ሲል በማንዋል ይሰጥ እንደነበር አስታውሰው አሰራሩን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ ታስቦ "ወረዳ ኔት" በተሰኘ ቴክኖሎጂ አገልገሎቱ መጀመሩን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ከማስቀረት ባሻገር ቀልጣፋ አሰራርን ለመዘርጋት ታልሞ የተዘጋጀ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የቴክኖሎጂው መሰረተ ልማት ላይ ባጋጠመው ጊዜያዊ ችግር ምክንያት አገልግሎቱም መስተጓጎሉን ጠቅሰው ዘላቂ መፈትሄ ለማበጀት ከሚመለከታቸው አካላት የኔትዎርከ መሰረተ ልማት ከማስተካከል ጎን ለጎን የተሻለ አቅም ያለውና የቀጥታ ዳታ ማዕከል የኔትዎርክ መሰረተ ልማት የማልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የተፈጠረው ችግር እስኪፈታ በጊዜያዊነት በማንዋል እንዲሰራ እየተደረገ ነው ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ ከአገልግሎት ፈላጊዎች ቁጥር አንፃር በቂ ምላሽ አለመሰጠቱን አምነዋል።

በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ አጋጣሚውን ተጠቅመው ችግር እየፈጠሩ ያሉ ህገ ወጥ ደላሎችን ለመቆጣጠር ኤጀንሲው ከጸጥታ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

በተጀመረው የክትትል ስራም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ አንድ እና ሁለት በሚባሉ አካባቢዎች 7 ህገ ወጥ ደላሎች ሰሞኑን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመው ቁጠጥሩ ተጠናክሮ የቀጥላል ብለዋል።

ኤጀንሲው ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ እየጠየቀ ቴክኖሎጂው ዳግም ስራ እስከሚጀምር ተገልጋዮች ባለው የማንዋል አገልግሎት አማራጭ እየተገለገሉ በትእግስት እንዲጠባበቁ አቶ መላክ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም