የኢትዮጵያን ፈጣን መንገድ ሽፋን 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ፈጣን መንገድ ሽፋን 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታቅዷል

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2014 /ኢዜአ/ በአስር ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያን የፈጣን መንገድ ሽፋን 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው።
ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ስኬታማ ስራዎችን ለማከናወን የአስር ዓመት እቅዶችን አዘጋጅታ እየተገበረች ትገኛለች።
መሪ የልማት ዕቅዱን መሰረት በማድረግ ተቋማት እቅድ አውጥተው እየተገበሩ ይገኛሉ።
ከዘርፎቹ መካከል በ2022 ዓ.ም የፈጣን መንገድ ሽፋን አሁን ካለበት ሶስት መቶ ኪሎ ሜትር ወደ 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር ለማድረስ አቅዳ እየሰራች መሆኑ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ መንገድ አስተዳደር የመንገድ አውታር እቅድ ቡድን መሪ ሳድያ በሽር ለኢዜአ እንደገለጹት ፈጣን መንገዶች የምጣኔ ኃብትና ማህበራዊ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ትልቅ ፋይዳ አላቸው።
አገራዊና አህጉራዊ ንግድና ምጣኔ ኃብት ትስስርን ለማቀላጠፍ ከመሰረታዊ መንገድ በተጨማሪ የፈጣን መንገዶች ሚና ትልቅ እንደሆነም አክለዋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን በፈጣን መንገድ ግንባታ ዘርፍ የሞጆ-ሓዋሳ እና አዲስ-አዳማን ጨምሮ እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ የፈጣን መንገድ ሽፋን 301 ኪሎ ሜትር መድረሱን አውስተዋል።
በአስር አመት እቅዱ ከ1 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር በላይ ፈጣን መንገድ በመገንባት አጠቃላይ የፈጣን መንገድን ሽፋን 1 ሺህ 600 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ነው ወይዘሮ ሳድያ የገለጹት።
በሌላ በኩል በፈጣን መንገድ መሰረተ ልማት ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር በማስተሳሰር የምጣኔ ኃብታዊ ውህደትን ለማሳለጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ከጂቡቲ፣ ከኤርትራና ከሱዳን ጋር ኢትዮጵያን የሚያገናኙ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት መታሰቡንም ገልጸዋል።
በተለይም ከሚኤሶ-ድሬ ደዋ ፈጣን አስፋልት መንገድ ለመገንባት ከዓለም ባንክ ጋር ሂደቱ አልቆ ውሳኔ እየተጠበቀ ነውም ብለዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያና የኬንያ የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር በሞያሌ የተገነባው የጋራ ኬላም ሌላኛው የትስስሩ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአስር አመቱ መሪ የልማት ዕቅድ መነሻ ነጥቡን በ2022 ዓ.ም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን ርእይ ይዞ የተዘጋጀ ነው።
የአፍሪካን ምጣኔ ኃብትና ንግድ ትስስር ለማጠናከር በዘላቂ የልማት ግብ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል መንገድ መሰረተ ልማት አንዱ ነው።