የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ተጠናቀቀ

535

መጋቢት 04 ቀን (ኢዜአ) የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መጠናቀቁን የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለፁ።

ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን በማሳለፍ በስኬት ተጠናቋል።

የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ጉባኤው ባለፉት አራት ዓመታት የተመዘገቡትን ለውጦችና የተከሰቱ ውጣ ውረዶችን አልፎ የተካሄደ ታሪካዊ ጉባኤ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉባኤው በሀገራዊ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ መምከሩን ያነሱት ኃላፊው፤ በተለይም ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ የተመዘገቡ ውጤቶችን እና የታዩ ክፈተቶችን በመገምገም ለውጡን አጠናከሮ ለመቀጠልና የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ለመስራት ወስኗል ብለዋል።

በአስተሳሰብ በአመራር እና በአደረጃጀት የኢትዮጵያንና የህዝቡን ፍላጎት የሚመልስ ፓርቲን መገንባት ላይም ትኩረት አድርጎ መምከሩን ተናግረዋል።ለዚህም የሚያግዙ የፓርቲውን ፕሮግራምና ህገ ደንብ በዝርዝር ከመከረባቸው በኋላ ማጽደቁን ተናግረዋል።

በሀገራዊ ለውጡ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ማስፋት፣ የህዝቡን ችግሮች መቅረፍ፣ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በመለወጥ የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም በተግባር በሚያስጠብቅ መንገድ ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ ጉባኤው አቅጣጫ አስቀምጧል ነው ያሉት።

ባለፉት አራት ዓመታት የታዩት የለውጥ ጭላንጭሎች በተግባር ተጠናከረው እንዲቀጥሉ ውሳኔ መተላለፉን በማንሳት አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲሰራ፣ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት እንዲፈጥርም አቅጣጫ መቀመጡን አንስተዋል።

ጉባኤው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ትላልቅ የሚባሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም ዶክተር ቢቂላ ተናግረዋል።ለዚህም የብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላት ሌት ተቀን መስራት እንደሚገባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

በአገራችን የተለያዩ አካበቢዎች የሚስተዋሉ ፅንፈኝነትና የዜጎች ጉዳት መፈናቀል እንዲቆም አመራሩ ልዩ እቅዶችን አውጥቶ መስራት እንዳለበትም መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል በሰለጠነ መንገድ ለማካሄድ የሚደረጉ ጥረቶችን ስኬታማ ለማድረግ የፓርቲው አመራርና አባላት ያለምንም እረፍት መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካም ፓርቲው አጥብቆ እንዲሰራ ውሳኔ ተላልፏል ነው ያሉት።

በጉባኤው ስምምነት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ሌብነትን የማይሸከም ስርዓት መገንባት መሆኑን ያነሱት ዶክተር ቢቂላ፤ ዜጎችን የሚያንገላታ አገልግሎት አሰጣጥን መቀየር፣ በአቋራጭ ለመክበር የሚሞክሩ አካላትን መታገል የብልፅግና አመራሮችና አባላት ቀዳሚ ተግባር እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት።

በዚህም ሌብነትን የማይሸከሙ ተቋማትን ለመገንባት በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።

የአገራችንን ኢኮኖሚ ካለበት የስርዓት ስብራት የተነሳ ዜጎችን በኑሮ ውድነት እየፈተነ በመሆኑ የኢኮኖሚ መዛባቱን በማስተካከል በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ሰላም የሚፈታተኑ የውጭና የውስጥ ኃይሎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡንም አብራርተዋል።

ዜጎችን የሁለንተናዊ ብልጽግና ተጠቃሚ ለማድረግ የፓርተው አባላትና አመራሮች በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል።ብልፅግና ፓርቲ ይዞት የተነሳውን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ጉዞ መላው ኢትዮጵያውያንም እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል ብለዋል።

ጉባኤው ለሚቀጥሉት ዓመታት ፓርቲውን የሚመሩ አመራሮችን፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የኢንስፔክሽንና የስነ-ምግባር ቁጥጥር ኮሚቴ አባላትን መምረጡንም ተናግረዋል።

በዚሁም መሰረት የብልፅግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና የሚያረጋገጥ ጠንካራ አመራር የመፍጠር ዋና መርህ ስኬታማ የሚያደርጉ 225 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መመረጣቸውን ገልጸዋልምርጫውም ዴሞክራሲያዊና አካታች እንደነበር ያነሱት ዶክተር ቢቂላ፤ ማዕከላዊ ኮሚቴው ኢትዮጵያን የሚመስል ሆኖ መመስረቱን ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱን ምርጫ ተከትሎ የፓርቲው 45 ስራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባላትም ተመርጠዋል ብለዋል።የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱም ኢትዮጵያን የሚገልጹና ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ አባላት የተካተቱበት ነው ብለዋል።በአጠቃላይ ጉባኤው በተነሱ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ የፓርቲውን አመራርና አባላት እንዲሁም የጉባኤውን የጋራ ውሳኔ የሚያንጸባርቁ የአቋም መግለጫዎች በማውጣት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም