የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ

329

መጋቢት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሥርዐተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

ብፁዕነታቸው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ዕውቀትን በመቅሰም አገልግሎት ሰጥተዋል።

በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና  ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት እና የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት የሃማኖቶች ተቋማት መሪዎችና ምዕመናን  በተገኙበት ነው።

ብፁዕ አቡነ መርቆሪዎስ  በቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረታቦር አውራጃ በአንዳቤት ወረዳ አረጊት ኪዳነ ምሕረት ልዩ ስሙ "ማር ምድር" በተሰኘው አካባቢ ከአባታቸው ከብላታ ፈንታ ተሰማና ከእናታቸው ከወይዘሮ ለምለም ገሰሰ በ1930 ዓ.ም ተወለዱ።

እድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ በአካባቢው ከሚገኙት ከመሪጌታ ላቀው ንባብና ዳዊት ከተማሩ በኋላ በአጭቃን ኪዳነምሕረት ደብር ምዕራፍና ጾመ ድጓን ተምረዋል።

ትምህርታቸውን ለማስፋፋትም ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ሄደው ለሁለት ዓመት ጎንጂ ቴዎድሮስ ገዳም ከመሪጌታ ወርቁ፤ ወደ ዋሸራ መንክር ሃይላ ቅድስት ማርያም በመሄድም ስመ-ጥር ከነበሩት ከታላቁ ሊቅ ከመሪጌታ ማዕበል ፈንቴ  ሁለት ዓመት፤ በጠቅላላው አራት ዓመት በመማር የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

ከዚያም ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ተመልሰው በደብረታቦር አውራጃ እስቴ ወረዳ አጋጥ ጽዮን ደብር ከመሪጌታ ሙጨ ላቀ የምዕራፍ ጾመ ድጓና የድጓ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

ቅዱስነታቸው በነበራቸው ከፍተኛ የትምሀርት ፍላጎት ወደ አቋቋም ቤት በመግባት መነጉዘር በሚባለው ደብር ከመሪጌታ ሚናስ ለሁለት ዓመት የአቋቋም ትምህርት ተምረዋል።

ከዚያም ቁት አቡነ አረጋዊ ደብር ከመሪጌታ ውብ አገኝ ለአንድ ዓመት ዝማሬ መሥዋዕትን የተማሩ ሲሆን ወደ ደብረ ታቦር አውራጃ ተመልሰው ከጥንቱ መምህራቸው ከመሪጌታ ሙጨ ላቀ ዘንድ የድጓ ትምህርታቸውን በመቀጠል ጽፈውና አመልክተው ከጨረሱ በኋላ፣ በነፋስ መውጫ አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው በስመጥሯ በቤተልሔም አራት ዓመት ቆይተው ድጓ አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀዋል።

የድጓ ትምህርታቸውን ካስመሰከሩ በኋላ ወደተወለዱበት ገዳም ሄደው በአረጊት ኪዳነምሕረት ገዳም ለሰባት ዓመታት ያህል ድጓ አስተምረዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዎስ፣ ሥርዓተ ምንኩስናን ከመምህርነት ጋራ አጣምሮ ለመያዝ ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ ስለሆነ በጣና ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ በመግባት ማዕረገ ምንኩስናን ከመምህር ኃይለ ማርያም በ1961 ዓ.ም ከተቀበሉ በኋላ በዚሁ ዓመት ማዕረገ ቅስናን ከጎጃም ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡

የገዳምን ሥነ-ሥርዓት ይበልጥ ማጥናት ስለፈለጉ፣ በባሕር ዳር አውራጃ ልዩ ስሙ ጋሾላ በተባለ ገዳም ገብተው የገዳሙን ሥነ-ሥርዓት እያጠኑና ለገዳማውያን እየታዘዙ ለሁለት ዓመት ገዳሙን ረድተዋል።

በገዳሙ በነበሩበት ጊዜ በጸሎተ ማኅበር፣ የልማት ሥራ በመሥራትና አቅመ ደካሞችን በመርዳት ገዳሙን አገልግለዋል።

ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በቅዳሴና በማሕሌት እያገለገሉ ትርጓሜ ሐዲሳትንና አቡሻኽርን ተምረዋል።

ዘመናዊ ትምህርታቸውንም በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ተከታትለዋል፡፡ በተጨማሪም ለመምህራን፣ የተደረገውን የስብከት ዘዴ ኮርስ ለሁለት ዓመታት ተምረው የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።

ባላቸው በቂ የቤተክርስቲያን ዕውቀትና ባሳዩትም የመንፈሳዊ አገልግሎትና የሥራ ወዳድነት ቤተ ክርስቲያናችን ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም ባደረገችው የ13 ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምእመናን በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው የኦጋዴን አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው ተሹመዋል።

በዚህ አውራጃ፣ በጠላት ፈርሶ የነበረውን ቤተክርስቲያን በማሠራትና በማሳደስ በጦርነት ምክንያት የተሸበረውንና የተደናገጠውን ሕዝብ በማጽናናት ስለ ኢትዮጵያ አገሩ ፍቅር በማስተማርና በማስረዳት ሐዋርያዊ ተልዕኳቸውን ፈጽመዋል።

ብፁዕ አቡነ መርቆሪዎስ በ1971 ዓ.ም ወደ ጎንደር ሀገረስብከት ተዛውረው በርካታ አባታዊና መንፈሳዊ ተግባራትን አከናውነዋል።

በወቅቱ በነበረው አለመረጋጋት በጭልጋና በደባርቅ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ሕዝቡን በማስተማር ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።

ብፁዕነታቸው በየጊዜው በሚያሳዩት መልካም የሥራ ውጤት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ተቀብለዋል።

በሀገረስብከት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤን በማቋቋምና በማጠናከር፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት ቅርሶችን በእንክብካቤ እንዲያዙ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ለሕዝበ ክርስቲያን እንዲደርሱ፣ የቤተክርስቲያን መመሪያና ደንብ ቃለ ዐዋዲ በተግባር እንዲተረጎም አድርገዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ አራተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት ነሐሴ 29 ቀን 1980 ነበር።

በፖለቲካዊ ግፊትና ጫና ከሀገራቸው ከመውጣታቸው በፊት መንበራቸውን እስከ ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም ድረስ ለቤተክርስቲያኗ አጠቃላይ አመራር ሲሰጡ ቆይተዋል።

ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ስድስተኛው የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ብፁዓነ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና የእምነቱ ተከታዮች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ቤተክርስቲያኗም የሁለቱንም ቅዱሳን ፓትርያርኮች በጸሎቷ እየጠራች በእኩል የአባትነት ክብር አስቀምጣ በየድርሻቸው እንዲያገለግሉና እንዲመሯት አድርጋ ቆይታለች።

ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆሪዎስ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በአርምሞና በጸሎት ቆይተው ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ84 ዓመታቸው የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም.ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

ሥርዓተ ቀብራቸውም ዛሬ መጋቢት 04 ቀን 2014 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

ብፁዕነታቸው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ዕውቀትን በመቅሰም አገልግሎት ሰጥተዋል።

የብፁዕነታቸው ሥርዐተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቃነ ጳጳሳት፣ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የተለያዩ ሀገራት የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ተፈፅሟል።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በ1980 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ተብለው በመሾም ላለፉት 34 ዓመታት አባታዊ አገልግሎት ሰጥተዋል።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቤተክርስቲያኗ ትምህርት የሆኑትን አቋቋም፣ ድጓና ዝማሬ መዋስዕት በላቀ ሁኔታ የተማሩ መሆናቸውን ሕይወት ታሪካቸው ይናገራል።

ብጹዕነታቸው ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም አርፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም