የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ፓትርያርክ ዘ-ኢትዮጵያ ስርዓተ ቀብር እየተካሄደ ነው

136

መጋቢት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ፓትርያርክ ዘ-ኢትዮጵያ ስርዓተ ቀብር በቅድስት ስላሴ ካቴደራል ቤተክርስቲያን እየተካሄደ ይገኛል።

የብፁዕነታቸው ስርዓተ ቀብር የቤተክርስቲያኗ ስርዓተ ቀኖና በሚያዘው መልኩ እየተከናወነ ነው።

በቅድስት ስላሴ ካቴደራል ቤተክርስቲያን እየተከናወነ በሚገኘው የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ አባቶች፣ የሌሎች አገራት ጳጳሳት እና ህዝብ ክርስትያኑ ተገኝተዋል።

ስርዓተ ቀብራቸውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ እንደሚፈጸም ይጠበቃል።

የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በ1980 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ተብለው በመሾም ላለፉት 34 ዓመታት አባታዊ አገልግሎት ሰጥተዋል።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቤተክርስቲያኗ ትምህርት የሆኑትን አቋቋም፣ ድጓና ዝማሬ መዋስዕት በላቀ ሁኔታ የተማሩ መሆናቸውን ሕይወት ታሪካቸው ይናገራል።

ብጹዕነታቸው ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም አርፈዋል።

የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የስንብት መርሃ ግብር ትናንት በመስቀል አደባባይ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም