የደቡብ አፍሪካው 'አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ' ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ይፈልጋል

100

መጋቢት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ አፍሪካው 'አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ' (ኤ ኤን ሲ) ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ፍላጎት እንዳለው የፓርቲው ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባል ፕሮፌሰር ኢቅባል ጃዝብሃይ ተናገሩ።

የደቡብ አፍሪካ 'አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ' ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ አባል ፕሮፌሰር ኢቅባል ጃዝብሃይ በበልጽግና ፓርቲ 1ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም የብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር የደረሰው ሥምምነት ታሪካዊና ፓርቲያቸው በአድናቆት የሚመለተው መሆኑን ጠቁመዋል።

''በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የጋራ የሰላምና የወዳጅነት ሥምምነት የአፍሪካ ቀንድ አገራት መሪዎች ለሰላምና ለደኅንነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል'' ብለዋል።

ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ መንግሥት ካቢኔ ሚኒስትሮች 50 በመቶ ሴት መሆናቸውንና ግዙፉ የኃይል ማመንጫ (የታላቁ ህዳሴ ግድብ) መገንባት መቻሉንም አድንቀዋል።

ይህም ኢትዮጵያና መላው አፍሪካ የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው ከመወሰን ወደ ኋላ የሚያስቀራቸው ምንም አይነት ችግር አለመኖሩን የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንትና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንዲሁም በካቢኔያቸው አመራር አገራዊ ምክክር ለማካሄድ መወሰኑም በአድናቆት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በተለያዩ የዓለም አገራት የተካሄዱት የ "በቃ" #NOMORE እቅስቃሴም ጦርነት ለሚናፍቁ አገራት ትልቅ መልዕክት መስጠቱን ጠቁመዋል።በተለይም ደግሞ ማንም አገር በኢትዮጵያ ላይ ፍላጎቱን መጫን እንደማይችል አመላካች ነው ብለዋል።

በተጓዳኝም እንቅስቃሴው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተከፈተባትን ሃሰተኛ ትርክትን ለመመከት ያደረገችው ትግልና የጽናት ምልክት ሆኖ እንደሚቆጠር ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች አዎንታዊ ስኬቶችን ያስመዘገበ ተስፋ ያለው ፓርቲ መሆኑን ጠቁመው አሁን ከሚያካሂደው ጉባኤ ብዙ ይጠበቃል ብለዋል።

ፓርቲያቸውም አሁን ተለዋዋጭ ከሆነው የዓለም ጂኦ ፖለቲካዊ ለውጥ አንጻር ብልጽግና የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች በንቃት እየተከታተለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም ፓርቲያቸው ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ዝግጁ መሆኑን ፕሮፌሰር ኢቅባል ጃዝብሃይ አረጋግጠዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የሚያካሄደው ጉባኤ የተሳካ እንዲሆንም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም