አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን የሁላችንም ቀና ትብብርና የጋራ ጥረት መኖር አለበት

203

መጋቢት 2/2014 (ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን የሁላችንም ቀና ትብብርና የጋራ ጥረት መኖር አለበት ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ ላይ በተጋባዥነት የውጭና የአገር ውስጥ እንግዶች እንዲሁም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በጉባኤው የፓርቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ፤ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች መሻገሯን አንስተዋል።

በተለይም ባለፉት 3 አመታት በርካታ ውጣ ውረዶችን በማለፍ ዛሬ ላይ መድረሷን አንስተዋል።

”የሁላችንም ራዕይ አንድና አንድ ነው እሱም በሀገራችን ሰላም ሰፍኖ የተረጋጋችና የለማች ኢትዮጵያን ማየት ነው” ብለዋል በመልእክታቸው።

በመሆኑም ትላልቅ ውሳኔዎችን የሚፈልጉ ጉዳዮች ከት ያሉ በመሆኑ ”በታሪክ አጋጣሚ በመገኘት ሀገርንና ህዝብን የመታደግ ሃላፊነት በእጃችን ወድቋል” ብሏል።

“ከትናንት የሚበልጥ ነገን ማየት ከቻልን ያቀድነውን ሁሉ ማሳካት እንችላለን” ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በምርጫም ሆነ በመንግስታዊ አሰራር ሊፈቱ ባልቻሉ መሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ለመምክር የቅድመ ምክክር ዝግጅቶችን እያደረገች መሆኑ መልካም የሚባል ውሳኔ እንደሆነም አንስተዋል።

አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ልሂቃን፣ ምሁራንና ሌሎችም በንቃት መሳተፍ አለባቸው ነው ያሉት።

ምክክሩ የህዝብን ባህልና እሴት ባማከለ መንገድ በመደማመጥና የጋራ መፍትሄ ለማስገኘት በሚያስችል መልኩ ሁሉንም ወገኖች ባሳተፈ መልኩ መካሄድ ይኖርበታል ብለዋል።

”አብሮነትን በልዩነታችን ውበት ለማረጋገጥ በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ በመምከር ችግሮችን እያቃለሉ በጋራ መጓዝ አማራጭ የለውም” ሲሉም ተናግረዋል ዶክተር ራሄል።

አገራዊ ምክክሩን የተሳካ ለማድረግ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና ድርብ ሃላፊነት ስላለበት ሚናውን በአግባቡ መወጣት አለበት ብለዋል።

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚጠበቅባቸውን ሚና በመወጣት ለአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ ስኬት መስራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።