በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሀይማኖት አባቶች ድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

214

መጋቢት 2/2014/ኢዜአ/ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሀይማኖት አባቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጠየቀ፡፡

በአዲስ አበባ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አዘጋጅነት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሀይማኖት አባቶች ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።

በቢሮው የስርአተ ጾታ ማስረጽ እና ማካተት ዳይሬክተር አቶ ጸሀዬ ብርሀኑ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ ከሀይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈለገው የበለጠ ማሕበረሰቡን ለማንቃት ታስቦ ነው።

በተለይም በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን የሚጸየፍ ትውልድ ለመፍጠር የሀይማኖት አባቶች ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።

የሀይማኖት አባቶች በየእምነታቸው ሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት የሚያወግዝ ትምህርት መስጠት እንዳለባቸውም አንስተዋል።

ሕዝቡ እሰፈላጊውን ግንዛቤ ከጨበጠ በኋላ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ከህግ አካላትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የሴቶችንና ህጻናትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር በመንግሥት ብቻ የሚከወን ተግባር በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ተቋማትና ግለሰቦች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የሀይማኖት አባቶች በበኩላቸው ለምዕመኑ አስፈላጊውን ግንዛቤ የሚፈጥር ስራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተወከሉት ቆሞስ አባ ፍቅረማሪያም ውይይቱ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል በጋራ ለመስራት እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል።

”የሀይማኖት አባቶች ይሄንን ሳንሰለች ማውገዝ እና ማስተማር አለብን” ብለዋል አባቶቹ።

የሴቶችና ህጻናት ጥቃትን አስከፊ ገጽታን የተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እንደሚያስተምሩ የተናገሩት ደግሞ ሀጂ አህመድ ሰኢድ ናቸው።

በእምነቱ አስተምህሮ ላይ እናቶች፣ ህጻናትና ሴቶች በአግባቡ ሊከበሩ እንደሚገባም ተመላክቷል ብለዋል።

ከዌንጌላዉያን ቤተክርስቲያናት ህብረት የተወከሉት ፓስተር ግርማ ቤካ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሴቶችና ህጻናት ለዚህ መሰሉ ጥቃት እንዳይዳረጉ ተግተው እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል።

ሀይማኖታዊ አስተምህሮ ሴቶችና ወንዶች መከባበርና በመተሳሰብ እንዳለባቸው ሰፍሮ ይገኛል ብለዋል።