ቋሚ ኮሚቴው የዘገዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቁ አሳሰበ

70

ዲላ፤ መጋቢት 2/2014 (ኢዜአ) አስፈጻሚው አካል የዘገዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለህብረተሰቡ ቅሬታ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት የደቡብ ክልል ምክር ቤት የከተማና መሰረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በቋሚ ኮሚቴው የተመራ ቡድን  በጌዴኦ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ሂደት የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በዚህ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ እንቁ ዮሐንስ እንዳሉት፤ በክልሉ በርካታ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች በምክር ቤቱ ይሁንታ አግኝተው በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ።

ሆኖም የግንባታዎቹ መዘግየት በተለይ በመንገድና የድልድይ ግንባታ ተጀምሮ አለመጠናቀቅ እንዲሁም የጥራት ችግር  ህብረተሰቡን  ለእንግልት እየዳረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ቀበሌን ከቀበሌ ፤ወረዳን ከወረዳ የሚያገናኝ የመንገድ መሰረተ መሰረተ ልማቶች ግንባታ መስተጓጎልን ጠቅሰዋል።

ይህም ወላድ እናቶችና የህክምና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አፋጣኝ እርዳታ እንዳያገኙ፤ ግብይትን ጨምሮ ለሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መንስኤ በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስነሳ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ችግሩን በዛላቂነት ለማቃለል  በክልል ደረጃ የዘገዩ ፕሮጀክቶች በመጠነኛ ወጪና በህብረተሰብ ተሳትፎ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደስራ መገባቱን ጠቁመው፤  ቋሚ ኮሚቴውም የተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በመዘዋወር ሂደቱ በምን ደረጃ እንደሚገኝ የመስክ ምልክታ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወናጎና ጎቾሬ ወረዳዎች በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድና የድልድይ ፕሮጀክቶች ተስፋ ሰጪ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የመንገድ ሰፋትና ጥራት እንዲሁም ከግንባታ ፍጥነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ውስንነቶች አፋጣኝ መፍትሄ ያስፈልገዋል ብለዋል

በክልሉ በየደረጃው የሚገኝ አስፈጻሚው አካል የዘገዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለህብረተሰቡን ቅሬታ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በዞኑ የዘገዩና ተጀምረው የቆሙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እየሆኑ መምጣታቸውን የተናገሩት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መሰረት መኩሪያ ናቸው።

ለህብረተሰቡ ጥያቄ አስፈጻሚው አካል አፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠናቀው አገልግሎት እስኪሰጡ ምክር ቤቱ ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የጌዴኦ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ የመንገድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ቢፍቱ በበኩላቸው፤ በዞኑ በ35 ሚሊዮን ብር በጀት  ከ85 ኪሎሜት በላይ መንገድና የአምስት ድልድዮች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና በወሰን ማስከበር ችግር፣ በበጀት እጥረትና በተቋራጭ አቅም ማነስ ግንባታዎቹ ከተቀመጠላቸው በላይ ጊዜ መውሰዳቸውን ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው የመስክ ምልከታ የህብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ የዘገዩ ፕሮጀክቶች የክልሉና የዞን ባለድርሻ አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተለይ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በክልል በጀት የሚሰሩ በመሆናቸው ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የክልሉ መንግስት ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ ኢሳያስ ጠይቀዋል።

ገላና ወንዝ ከዚህ በፊት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ክፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደነበረና ድልድይ ተሰርተው አገልግሎት በመስጠቱ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ  የኮቾሬ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ማሞ ሻሎ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም