በኢትዮጵያ የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ስጋት ስላለ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

204

መጋቢት2/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ስጋት ስላለ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ወረርሽኙ መከሰቱንና በኢትዮጵያ ስጋቱ ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በቅርቡም የኬንያ ጤና ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ በተለያዩ የኬንያ ወረዳዎች ወረርሽኙ መከሰቱን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በኡጋንዳ፣ ቻድ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ካሜሮን፣ ኮትዲቯርና ደቡብ ሱዳን መከሰቱን የቢጫ ወባ ቴክኒክ ቡድን አክሏል።

በቅርቡም በኢትዮጵያ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በቅርቡ ተከስቶ ዜጎችን ለሞትና ለህመም መዳረጉን ጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ጎረቤት አገራትን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራት የተከሰተው ወረርሺኝ ለኢትዮጵያም ትልቅ ስጋት እንደሆነ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

ኅብረተሰቡ በሽታው ተከስቶ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ጥንቃቄ እንዲያደረግ አሳስቧል።

ባለድርሻ አካላትም በሽታውን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ፣ የመከላከል ሥራዎችን በቅንጅት ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ጠቁሟል።

ኢንስቲትዩቱ በቅድመ መከላከል ሥራ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግ አስታውቋል።

የቢጫ ወባ ወረርሺኝ በመላው ዓለም  በየዓመቱ 200 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን እንደሚያጠቃና 30 ሺህ የሚሆኑትን ለሞት እንደሚዳርግ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የበሽታው ምልክት ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመም፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ እንዲሁም ድካምን ይጨምራል።