በሰው ማገት ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው

75

መተማ፤ የካቲት 2/2014(ኢዜአ ) በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ሰው በማገት ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የወረዳው ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

ግለሰቦቹ የካቲት 9/2014 ዓ.ም  ማታ አምስት  ተኩል አካባቢ በመተማ ወረዳ ኩመር አውላላ ቀበሌ  የኩመር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት ሴት መምህራንን ከቤታቸው  አግተው በመውሰድ የወንጀል ድርጊቱን መፈጸማቸውን  በማስረጃ እንደተረጋገጠባቸው ተመልክቷል።

የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ ወይዘሮ ትዕግሥት ተችሎ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አንደኛ ተከሳሽ  ማለደ አቡሃይና ሁለተኛ ተከሳሽ  ሰለሞን አሸተ ከሌሎች ካልተያዙ ሶስት  ተባባሪዎች ጋር በመሆን ነው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙት።

ይህም  የግል ተበዳይ ቤተሰቦችን ስልክ በመደወል 900 ሺህ ብር ካልከፈሉ እንደሚገድሏቸው በማስፈራራት ለሶስት ቀናተ  ካቆዩዋቸው በኋላ በድርድር 190 ሺህ ብር በመቀበል ለቀዋቸዋል።

የወረዳው የፀጥታ አካል ወንጀሉ ከተፈፀመ ጊዜ ጀምሮ ከማህበረሰቡ ጋር  ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ የካቲት 20/2014 ዓ.ም ሁለቱን ተከሳሾች ወደ ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ሊሄዱ ሲሉሲዘጋጁ  በገንዳ ውሃ ከተማ ተይዘዋል።

አጋቾቹ በእገታ ከተቀበሉት ውስጥ  180 ሺህ 450 ብር ጋር ይዘው እንደነበረም ወይዘሮ ትዕግሥት አስረድተዋል።

ግልሰቦቹ  በአቃቤ ህግ የቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የክስ መዝገቡን መርምሮ ተከሳሾች በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህግ ቁጥር 149/1 መሰረት የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቀዋል።

ትናንት በዋለው ችሎትም ጥፋተኞችን ያርማል፤ ሌሎችን ያስተምራል በማለት እያንዳንዳቸውን በ13 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን  የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪዋ ገልጸዋል።

በዚሁ ወንጀል የተሳተፉ ሌሎች ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችንም ፖሊስ ተከታትሎ ፍርድ እንዲያሰጥ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም