የጤና መረጃ ሳምንት በሚቀጥለው ሳምንት ይከበራል

85

መጋቢት 2/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የጤና መረጃ ሳምንት ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ ለአምስት ቀናት እንደሚከበር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የመረጃ ሳምንቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ እንደተገለጸው የቀኑ መከበር ዋና ዓላማ በጤናው ዘርፍ ያሉ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማሻሻልና ከአጋር አካላት ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር ነው።

በጤና ሚኒስቴር የፖሊሲ፣ እቅድ ክትትልና ምዘና ምክትል ዳይሬክተር አቶ መስዑድ መሀመድ እንደተናገሩት፤ የጤና መረጃ ስርዓትን ለማሻሻል እየሰራ ነው።     

ባለፉት ዓመታት በጤና መረጃ አያያዝ ላይ 'የመረጃ አብዮት ስትራቴጂያዊ እቅድ' በመንደፍ ወደ ስራ መገባቱንም አብራርተዋል።    

በዚህም በጤና መረጃ ምልዑነት ላይ ያለው አፈጻጻም እየተሻሻለ መምጣቱንና ይህንኑ ለማጠናከር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።    

አብዛኛው የጤና ተቋማት የካርድ አያያዝ ስርዓታቸውን ወደ ኤሌክትሮኒክ እንዲቀይሩ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ መስዑድ ይህም የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት እያሻሻለው መሆኑን ጠቁመዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ አክለውም፤ የጤናው ዘርፍ መረጃ ስርዓት ጥራትና ወጥነት ላይ የበለጠ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።  

ለዚህም ደግሞ የአጋር አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተው የጤና መረጃ ሳምንት ማክበር ያስፈለገበት ምክንያት ለዚሁ መሆኑም ያብራራሉ።  

በየደረጃው ያለው አመራር የመረጃ ስርዓቱን ማጠናከር ላይ ያለውን ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባው ማስገንዘብ ሳምንቱ የሚከበርበት ሌላው ዓላማ መሆኑንም ገልጸዋል።   

የመረጃ ተደራሽነትና ማጋራት ላይ የተዘጋጃውን መመሪያ ይፋ ማድረግና የፓናል ውይይቶችን ማካሄድ በሳምንቱ ከሚካሄዱ ሁነቶች መካከል መሆኑን ዘርዝረዋል።  

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ሚኒስቴሩ የጤናው ዘርፍ መረጃ ስርዓትን ለማጠናከር ከስድስት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር እየሰራ ነው።    

በዚህም በአቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምርና በስልጠናዎች ላይ በጋራ እየተሰራ መሆኑም አስረድተዋል።      

የመረጃ ሳምንቱ ከመጋቢት 5 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የሚካሄድ መሆኑም ተመልክቷል።     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም