አገራዊ ምክክሩ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ የምናመነጭበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው

75

መጋቢት 2/2014 (ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ ለጋራ ችግሮቻችን የጋራ መፍትሄ የምናመነጭበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ እድሉን ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሴት የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ባሉ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ለሚደረገው አገራዊ ምክክር በተለይም የሴቶች ተሳትፎ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ፖለቲካዊ ችግሮችንና ጫፍ የረገጡ ልዩነቶችን በውይይት በማርገብ ለትውልዱ የምትመች አገር ለመገንባት አገራዊ ምክክር ለማድረግ በሂደት ላይ ይገኛል።

አገራዊ ምክክሩን የሚመራ ኮሚሽን ተቋቁሞና ኮሚሽነሮችም ተሰይመውለት ለምክክሩ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆኑም ይታወቃል።  

በመሆኑም ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በተለይም የሴቶች የነቃ ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ከተለያዩ ተቋማት ኢዜአ ያነጋገራቸው ሴቶች ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ያልተገባ መካረርና ጥላቻ ረግቦ ሰላምና አብሮነት ሲጎለብት የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች ሴቶችና ህጻናት በመሆናቸው ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ተሳትፏችን ወሳኝ ነው ይላሉ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ሬጅስትራር ወይዘሮ የትነሽ ማሙሸት።

የተሻለች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ ጽንፍ ይዘን በምንናቆርባቸው አገራዊ ጉዳዩች በቅራኔዎቻችን ላይ ሁላችንም ተቀራርበን መመካከር አለብን ብለዋል።

ምክክር ማንኛውንም ችግር እንደሚፈታ አምናለሁ የሚሉት ወይዘሮ የትነሽ የተሻለች አገር ለመገንባት ለውይይትና ምክክር ትልቅ ሥፍራ መስጠት ይገባል፤ ለዚህም የሴቶች ተሳትፎ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥርዓተ ጾታ ጉዳይ ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ ኤቨሪና  ወልደመስቀል፤  የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በተለይም ለመልካም ዜጋ ግንባታና አገራዊ ልማት ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።

የሴቶች ተሳትፎ ሲነሳ የቤተሰብ፣ የማህበረሰብ፣ የአገር ግንባታ መሰረቶች በመሆናቸው በኢትዮጵያ ሊካሄድ ለተጀመረው አገራዊ ምክክር ውጤታማነት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ሜሮን ከበደ በበኩላቸው፤ በአገራዊ ምክክሩ ጉዳይ ተመሳሳይ ሐሳብ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ የምክክር መድረክ ሁላችንም ተሳትፈን ለጋራ አገራችን መሰረት የሚጥል የጋራ መፍትሄ የምናፈልቅበት መሆን አለበት ብለዋል።

በመሆኑም አገራዊ ምክክሩ ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትሄ የምናመነጭበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ በመሆኑ ለስኬቱ በጋራ መስራት አለብን ነው ያሉት።

ለዚህም በተለይም የሴቶች የነቃ ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በርካታ የዓለም አገራት የውስጥ ፖለቲካዊ ቅራኔያቸውን ለመፍታት ብሔራዊ ምክክርን የመፍትሔ አማራጭ አድርገው እንደተጠቀሙበት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም