ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶች መጠቀም ያስፈልጋል- ምሁራን

205

ሚዛን፣ መጋቢት 2/2014 (ኢዜአ)በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶች መጠቀም እንደሚያስፈልግ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ተናገሩ።

 ምክክሩ የሕዝቡን ባህልና ወግ መሠረት ባደረገ መልኩ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው የተመለከተው።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር አለማየሁ አብርሃም እንዳሉት፤ አሁን ላይ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋለው የሀሳብ ልዩነትና አለመግባባት የተረጋጋና የሰከነ ዴሞክራሲያዊሥርዓት የመገንባትን ሂደቱን አስቸጋሪ ስለሚያደርገው ከወዲሁ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል።

ለዚህ እውን መሆን ደግሞ ሀገራዊ ምክክር መድረኩ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፣ ለዚህም  ውጤታማነት ሀገር በቀል እውቀት፣ ጥበብ፣ ወግና የባህል እሴትን መሠረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ምክክሩ  የኢትዮጵያውያንን የአብሮነት እሴት ላይ በመመርኮዝ  ወደ ተግባር መግባት ከተቻለ ዓላማ ለማሳካት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን  ችግሮቻችንን ለመፍታት በየአካባቢው የሚገኙ የሽምግልናና የምክክር እሴቶችን መጠቀም ይገባናል ብለዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ጉዳይ መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚያግዝ በመሆኑ ተያይዞም  አንድነትን ለማጠናከር በሆደ ሰፊነት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ከዚህ አንፃር ምክክሩ ተግባራዊ ሲሆን ህዝብን በገለልተኛ ስሜት ማዳመጥ የኮሚሽኑ ቁልፍ ጉዳይ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ  በትክክለኛና እውነት ላይ ብቻ የተመሠረተ ምክክር በማስፈጸም ሀገሪቱ ከተጋረጠባት አደጋ ያሻግራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መምህር አለማየሁ ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ደረሰ ዳንኤል፤ ኢትዮጵያ የአብሮነትና መከባበር እሴት ማደስ የሚጠበቅባት ወቅት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ  ምክክሩ ገንቢ ሚና እንደሚኖረው  ገልጸዋል።

 ”ህዝብን ያማከለ ሰላምና አንድነትን ለመፍጠር የሚደረግ ምክክር በመሆኑም ነገሮችን ከሥር መሠረት ተመልክቶ ለመፍታት ጥሩ አጋጣሚ ነው” ሲሉ አመልክተዋል።

በሀገራዊ  ወግና ሥርዓት የተቃኘች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ባህላዊ እሴቶቿን አክብሮ መንቀሳቀስ  ከፖለቲከኞች አንስቶ ከሁሉም ማህበረሰብ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ባህሎች ሰላምን በሽምግልና በማጽናት፤ ጥልን በካሳና  በግሳጼ የመመለስ አቅም እንዳላቸው ያወሱት ምሁሩ፤ይህንን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ማዋል ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት ተሳስሮ  በመቆም ለሀገራዊ ምክክር መድረኩ ውጤታማነት የራሱን አሻራ ማኖር እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ባለፈው ወር 11 ኮሚሽነሮች የተሰየሙለት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ምክክር ለማድረግ በሂደት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።