የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በምስራቅ ባሌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ

77

ጎባ፤ መጋቢት 1/2014(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በምስራቅ ባሌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 6 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የእህልና ሌሎች ቁሶችን ድጋፍ አደረገ፡፡

ድጋፉን በዞኑ ዋና ከተማ ጊኒር ተገኝተው ያስረከቡት የክፍለ ከተማው አፈ ጉባኤ አቶ ሙሉጌታ አሰፋ ናቸው፡፡

አፈ ጉባኤው በወቅቱ እንዳሉት፤ ድጋፉ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መዲና መሆኗን በተግባር የሚያሳይ ነው፡፡  

''ኢትዮጵያዊያን በችግር ጊዜ የመረዳዳት የቆየ ባህል አላቸው'' ያሉት አፈ ጉባኤው፣ ችግሩ እስኪቃለል ድረስ ባለሃብቶችንና ነዋሪዎችን በማስተባበር ድጋፉ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ 120 ኩንታል የምግብ ዱቄት፣ በ13 ተሽከርካሪዎች የተጫነ የእንስሳት መኖና አልባሳትን ያካትታል፡፡

የምስራቅ ባሌ ዞን የአደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሀረግነሽ አለሜ፤ ክፍለ ከተማው ርቀት ሳይበግረው ለዞኑ ድርቅ ተጎጂዎች ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ለጋስ ድርጅቶች፣ባለሃብቶችና ሌሎች አካላት እህልና የእንስሳት መኖ ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀደም ሲልም በሁለቱ የባሌ ዞኖች በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች 78 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ መደረጉ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም